የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሀብቶች በኢትዮጰያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ
የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሀብቶች በኢትዮጰያ የኢንቨስትመንት ትኩረት መስኮች ማለትም በግብርና፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ ሀይል፣ ቱሪዝምና ማዕድን ፍለጋ እንዲሁም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ መቅረቡን በማድነቅ ሀገራቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደምታደርግ እና በኢንቨስትመንቱም በሰፊው እንደሚሰማሩ ገልጸዋል።
ባለሀብቶቹ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ትናንት ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደዉ የኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያዎች የቢዝነስ ፎረም ላይ ነዉ፡፡
በቢዝነስ ፎረሙ የኢትዮጵያ እና ከሳዑዲ ዓረቢያ የመጡ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች እንዲሁም ከ150 በላይ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።
መድረኩም የሀገራቱን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብና የሁለቱን አገራት የቢዝነስ ትስስርን የማጠናከር አላማ ያለው መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዳያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል፥ በፎረሙ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያና ሳዑዲ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መሰል የቢዝነስ ፎረም መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አህመድ አል ቃጣን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ሳዑዲ ዓረቢያ ከምንጊዜውም በተሻለ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሀገሪቱ እያካሄዱ ያሉት ማሻሻያ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚጋብዝ በመሆኑ የሳዑዲ ባለሀብቶችም እድሉን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ሲሆን አሁን ላይ በኢትዮጵያ 229 ፈቃድ ያላቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሃብቶች እንደሚገኙ ተገልጿል።
ምንጭ ኤፍቢሲ