ታላቁ የአረፋ ቀን መቼ ይውላል? በእለቱ የሚከናወኑ ተግባራትስ ምንድን ናቸው?
የአረፋ ቀን በሂጅራ አቆጣጠር የመጨረሻው ወር የሆነው ዙል ሂጃህ በገባ በዘጠነኛው ቀን ይውላል
በእለቱ የሃጂ ተጓዦች ወደ አራፋት ተራራ በመውጣት የተለያዩ ሃይማታዊ ስርዓቶችን ይፈጽማሉ
ሳኡዲ አረቢያ የዘንድሮው የኢድ አል አድሃ በዓል ሰኔ 9 2016 እንደሚከበር አስታወቀች።
በሂጅራ አቆጣጠር የመጨረሻው ወር ዙል ሂጃህም ከዛሬ ጀምሮ አንድ ተብሎ መቆጠር እንደሚጀምር ትናንት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
የአረፋ ቀን በዙል ሂጃህ ወር ዘጠነኛ ቀን እንደሚውል ይታወቃል። በመሆኑም ለሃጂ ወደ ሳኡዲ ያቀኑ ሙስሊሞች ከኢድ አል አድሃ በዓል አንድ ቀን ቀደም ብለው (ሰኔ 8) ወደ አራፋት ተራራ ይወጣሉ።
የአራፋት ተራራን መውጣት ለሃጂ ተጓዦች ልዩ ትርጉም አለው፤ የሀጂ ተጓዦች የምህረት፣ ይቅርታና ጸጸት እንዲሁም መስዋዕትነት ማሳያ በሆነው ቀን ተራራውን መውጣት ከፈጣሪ ጋር የመቀራረብ እድል ይሰጣል ብለው ያምናሉ።
ኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም ይከበራል።
አዳምና ሄዋን ከገነት ወጥተው ለረጅም ዘመናት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ በአራራት ተራራ ላይ መገናኘታቸው የሚዘከርበት በዓል መሆኑንም የሃይማኖቱ አባቶች ይናገራሉ።
የሃጂ ተጓዦች ከሚከውኗቸው አበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱና ወሳኙ የአራፋት ተራራን መውጣት ነው።
ከመካ በስተምስራቅ 20 ኪሎሜትር ርቆ የሚገኘውን ቅዱስ ተራራ መመልከትና ሃይማኖታዊ ስነርአቶችን በዚያው መፈጸም እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ያዛል።
የዘንድሮው የአረፋ ቀን ሰኔ 8 2016 የሚውል ሲሆን፥ በእለቱ የሃጂ ተጓዦች ከሚና ወደ አራፋት ተራራ ይወጣሉ።
ጽሀይ እስክትጠልቅ ድረስም ቅዱስ ቁርአን እያነበቡ፣ ፈጣሪን እያወደሱና እና የምህረት እጁን እንዲዘረጋ እየለመኑ ይቆያሉ።
የናሚራ መስጂድ ኢማም ስለአራፋት ቀን የሚሰጡት ሃይማኖታዊ አስተምህሮም በእስልምና ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።
የሃጂ ተጓዦች ጽሃይ ከጠለቀች በኋላም በመካ አካባቢ በሚገኘውና በርካታ ሰዎችን ማስተናገድ በሚችለው ሙዝዳሊፋህ በማቅናት ቀሪ ሃይማኖታዊ ስርአቶችን ከውነው ያርፋሉ።
ሙስሊሞች የመስዋዕትነት በዓሉን አረፋ እርድ በመፈጸም፣ በጋራ በመጸለይ እና ከፈጣሪ ምህረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን ያሳልፉታል።