ኢራናውያን ከዘጠኝ አመት በኋላ ለኡምራ ወደ ሳኡዲ አቀኑ
በቀጣይ 20 ቀናት ከ5 ሺህ በላይ ኢራናውያን ወደ መካ ይጓዛሉ ተብሏል
ሳኡዲ አረቢያ እና ኢራን ባለፈው አመት በቻይና አደራዳሪነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማደሳቸው ይታወሳል
ኢራናውያን የኡምራ ተጓዦችን ያሳፈረ አውሮፕላን ወደ ሳኡዲ ማቅናቱ ተነገረ።
ከዘጠኝ አመት በኋላ ከኢራን ወደ ሳኡዲ የተደረገው የኡምራ ጉዞ የሀገራቱ ግንኙነት መሻሻሉን ያሳያል ተብሏል።
በኢራን የሳኡዲ አምባሳደር አብዱላህ ቢን ሳውድ አል አንዚ በቴህራን አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለ85 የመጀመሪያው ዙር ተጓዦች ሽኝት አድርገዋል።
ኢራናውያኑ የኡምራ ተጓዦች በታህሳስ ወር 2023 ጉዞውን እንደሚያደርጉ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም “በቴክኒካዊ ችግሮች” ምክንያት መዘግየቱን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን የበረራ እና የማረፊያ ቅድመ ሁኔታዎች በመስተካከላቸው ጉዞው መጀመሩን ነው ያስታወቁት።
እስከ ግንቦት 10 2024 ድረስም ከ5 ሺህ በላይ ኢራናውያን ወደ መካ እንደሚጓዙ መገለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኢራን በመጋቢት ወር 2015 ሁለት ታዳጊ ዜጎቿ በጂዳ አውሮፕላን ማረፊያ ውክቢያና እንግልት ደርሶባቸዋል ካለች በኋላ የኡምራ ተጓዦችን ወደ ሳኡዲ አረቢያ መላክ ማቆሟ ይታወሳል።
ከዚህ እገዳ አንድ አመት በኋላም ሪያድ የሺያ የሃይማኖት አባት የሆኑትን ኒምር ባቂር አል ኒምር መግደሏና በቴህራን በሚገኘው የሳኡዲ ኤምባሲ ላይ ሁከት መፈጠሩን ተከትሎ ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማቋረታቸው አይዘነጋም።
ቻይና ባለፈው አመት መጋቢት ወር ሁለቱ የመካከለኛው ምስራቅ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለሰባት አመት ያቋረጡትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያድሱ ማድረጓ የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ዳግም እስኪያድሱ ድረስ ኢራናውያን ወደ ሳኡዲ ማቅናት የሚችሉት ለሃጂ ጉዞ ብቻ ነበር።
ኡምራ አቅሙ ያላቸው ሙስሊሞች በየትኛውም ጊዜ ሊያደርጉት የሚችሉት ሃይማኖታዊ ጉዞ ነው።