የሀገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግስት ካደረገ በኋላ በምያንማር የተፈጠረው አለመረጋጋት ተባብሷል
ወታደራዊውን መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም በምያንማር ላለፉት ሳምንታት የተቃውሞ ሰልፎች በመደረግ ላይ የቆዩ ሲሆን ዛሬ እሁድ እለት በመላው ሀገሪቱ በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ፖሊስ ጠንካር ያለ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል፡፡ በዛሬው የፖሊስ እርምጃ ቢያንስ 18 ሰዎች እንደተገደሉ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ፖሊስ በአስለቃሽ ጭስ እና ጥይቶችን ወደ ሰማይ በመተኮስ ሰልፈኞችን መበተን ሲሳነው ቀጥታ ሰልፈኞቹ ላይ መተኮስ እንደጀመረ የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል፡፡ ከሟቾቹ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውም ነው የተዘገበው፡፡
የሀገሪቱ ጦር ኃይል ባለፈው ህዳር ወር የተካሔደውን ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል ምክንያት ፣ በምርጫ የተመረጡትን የመንግሥት መሪ አውንግ ሳን ሱ ቺን እና አብዛኛውን አመራሮች እ.ኤ.አ. የካቲት 1 በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ምያንማር ትርምስ ውስጥ ትገኛለች፡፡
ከ 50 ዓመታት ገደማ ወታደራዊ አገዛዝ በኋላ ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይወስዳታል ተብሎ የታመነበት ጉዞ እንዲቆም ያደረገው መፈንቅለ መንግስት ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የምያንማር ዜጎችን ለተቃውሞ ወደ ጎዳና ሲያስወጣ የምዕራባውያን ሀገሮችን ውግዘትም አስከትሏል፡፡ የተለያዩ ተቋማትም መፈንቅለ መንግስቱን በማውገዝ ላይ ሲሆኑ ፣ ፌስቡክ እና ኢኒስታግራም የሀገሪቱን ወታደራዊ ባለስልጣናት ማገዳቸው ይታወሳል፡፡
በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የምያንማር ጦር የፈጸመውን መፈንቅለ መንግስት በጽኑ አውግዘዋል ፣ አንዳንዶችም በወታደራዊ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀቦችን መጣል ጀምረዋል፡፡ ከተለያዩ አካላት ጫናዎች የበረቱበት የሀገሪቱ ጦር አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ሁኔታዎችን አመቻቻለሁ ቢልም በብዙዎች ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የሳን ሱ ቺ ፓርቲ ደጋፊዎች ፣ ፓርቲው በሰፊ ልዩነት ያሸነፈበት የመጀመሪያው ምርጫ ውጤት እንዲከበር ይፈልጋሉ፡፡