በ ምያንማር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተካሔደ
ወታደራዊው ቡድን ከ 2 ወራት በፊት የተካሔደው ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል ነው በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው
የሀገሪቱ መሪ ኦንግ ሳን ሱ ቺ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ታስረዋል
የምያንማር ጦር ዛሬ ማለዳ የሀገሪቱን መሪ ኦንግ ሳን ሱ ቺን እና ሌሎች ፖለቲከኞችን በማሰር ስልጣን ተቆጣጥሯል፡፡
እርምጃውን ተከትሎ የሀገሪቱ ጦር በራሱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባስተላለፈው መልዕክት ከምርጫ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የሀገሪቱን ቁልፍ የፖለቲካ መሪዎች ማሰሩን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታውቋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው የጦሩ መሪ ሚን ኦንግ ህላይንግ ሀገሪቱን የመምራት ኃላፊነትን ተረክበዋል፡፡
በሀገሪቱ መፈንቅለ መንግስት የተካሔደው ፣ ከሁለት ወራት በፊት የተካሔደውን ምርጫ ተከትሎ በወታደራዊው ቡድን እና በሲቪል ፖለቲከኞች መካከል ለብዙ ቀናት የፖለቲካ ውጥረት ነግሶ ከቆየ በኋላ ነው፡፡ በምርጫው የኦንግ ሳን ሱ ቺ ፓርቲ ፣ ናሺናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ ፣ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን የፓርላማ መቀመጫ ያገኘ ሲሆን አዲሱ መንግስት ሊመሰረት ሰዓታት ሲቀሩት ነው ወታደሩ ስልጣን መቆጣጠሩን ያወጀው፡፡
ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ የምያንማር ዋና ዋና የዜና ቻናሎች ከአየር ተቋርጠዋል፡፡ በሀገሪቱ ኢንተርኔትም መቋረጡን ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡
በህዳር ወር የተካሔደው ምርጫ ስለመጭበርበሩን በሀገሪቱ ጦር የቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ የማጣራት ስራ ካልተከናወነ መፈንቅለ መንግስት ሊደረግ እንደሚችል የጦሩ ቃል አቀባይ ባለፈው ሳምንት ገልጸው እንደነበር ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2011 ነበር በምያንማር ወታደራዊ አገዛዝ አብቅቶ በዲሞክራሲ ሽግግር የሲቪል መንግስት የተመሰረተው፡፡ በወቅቱ የተካሔደውን ምርጫ የ ሱ ቺ ፓርቲ 83 በመቶ በማሸነፍ ስልጣን ሲመሰርት ፣ ወታደራዊው ዩኒየን ሶሊዳሪቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ፓርቲ ከ476 የፓርላማ መቀመጫዎች 33 ብቻ ነው ያሸነፈው፡፡
በህዳር ወር የተካሔደውን ምርጫም የ ሱ ቺ ፓርቲ ሲያሸንፍ ወታደራዊው ቡድን ያቀረበውን አቤቱታ የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ውድቅ አድርጓል፡፡
ይህን ተከትሎ በርማ በመባልም በምትታወቀው ምያንማር የተፈጸመውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት አውግዘዋል፡፡