አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸንፈች
ትግራይ ክልል የምትገኘው አትሌት ሌተሰንበት ግዴይ በክልሉ ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በውድድሩ መሳተፍ አልቻለችም
በወንዶቹ ኬንያዊው ኪቢዎት ካንዲ ክብረወሰን በመስበር አሸንፏል
አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸንፈች
አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ዛሬ በቫሌንሺያ የተካሄደውን የግማሽ ማራቶን ውድድር በአሸናፊነት አጠናቀቀች።
አትሌቷ በርቀቱ ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ ሲሆን ግማሽ ማራቶኑን ያጠናቀቀችው በ 1፡05፡18 ሰዓት ነው፡፡ ገንዘቤ ውድድሩን የጨረሰችበት ሰዓቱ እስካሁን በርቀቱ የመጀመሪያ ተሳትፎ የተመዘገበ ፈጣን ሰዓት እንደሆነ ሱፐር ስፖርት ዘግቧል፡፡
ሌለኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ርቀቱን 1፡05፡51 ሰአት በማጠናቀቅ ውድድሩን በ3ኛ ደረጃ ጨርሳለች፡፡
ውድድሩን 2ኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ደግሞ ኬንያዊቷ ሼይላ ቼፕኩሪ ናት፡፡
በወንዶቹ ምድብ ደግሞ የበቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶንን ኬንያዊው ኪቢዎት ካንዲ ክብረወሰን በመስበር አሸንፏል፡፡ ካንዲ ውድድሩን 57 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ያጠናቀቀ ሲሆን በሀገሩ ልጅ ጂዮፍሪ ኪፕሳንግ ካምዎሮር በ58፡01 ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረወሰን በ29 ሰከንድ አሻሽሏል፡፡
ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ያጠናቀቀው ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ ሲሆን 3ኛ እና 4ኛ ሆነው ያጠናቀቁት ደግሞ ኬንያውያን ናቸው፡፡ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው የጨረሱት አራቱም አትሌቶች ክብረወሰን አሻሽለዋል፡፡ ለዚህም የቫሌንሺያ የአየር ሁኔታ ምቹ መሆን በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡
በ 5000 ሜ. እዛው ቫሌንሺያ በተካሔደ ውድድር በቅርቡ የዓለምን ክብረወሰን የያዘችው አትሌት ሌተሰንበት ግዴይ ትግራይ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በክልሉ የምትገኝ በመሆኗ በዛሬው የግማሽ ማራቶን መሳተፍ አልቻለችም፡፡