ስፖርት
አትሌት ለተሰንበት ግደይ በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት ከቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ውጭ ሆነች
በቅርቡ አዲስ የ5 ሺ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ማስመዝገቧ ይታወሳል
ለተሰንበት ከውድድሩ ውጭ የሆነችው በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የምትገኝ መሆኗን ተከትሎ ነው
አትሌት ለተሰንበት ግደይ በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት ከቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ውጭ ሆነች
ከነገ በስቲያ እሁድ በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎዋን እንደምታደርግ ስትጠበቅ የነበረችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከውድድሩ ውጭ መሆኗ ተገለጸ፡፡
ለተሰንበት በውድድሩ ብርቱ ፉክክርን እንደሚያደርጉ ከሚጠበቁት ከእነ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ እና ከኬንያዊቷ ሼይላ ኬፕቹሩይ መካከል ነበረች፡፡
ሆኖም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የምትገኝ መሆኗን ተከትሎ ከውድድሩ ውጭ ሆናለች፡፡
በህወሓት እና በፌዴራል መንግስት መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በትግራይ የጉዞም ሆነ ሌሎች የግንኙነት መንገዶች መቋረጣቸው እና ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ለተሰንበት በቅርቡ በዚሁ በቫሌንሺያ ከተማ በተካሄደ የ5 ሺ ሜትር ውድድር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው፡፡
መረጃው የአፍሪካ አትሌቲክስ ዩናይትድ ነው፡፡