አየር መንገዱ ሽልማቱን ለተከታታይ 3ኛ ጊዜ ነው ያሸነፈው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማትን ለ3ኛ ጊዜ ተቀዳጀ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓመቱ (እ.ኤ.አ 2020) ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማትን ተቀዳጀ፡፡
ሽልማቱን የተቀዳጀው የግብጽ፣የኬንያ፣ የደቡብ አፍሪካ እና ሌሎችንም የአህጉሪቱን ተፎካካሪ አየር መንገዶች በማሸነፍ ነው፡፡
በአቪዬሽኑ ዘርፍ ያሳየው ድንቅ አፈፃፀም እና ስኬት ለአሸናፊነት አብቅቶታል እንደ አወዳዳሪው “አለም አቀፍ የጉዞ ሽልማት” (World Travel Awards) ገለጻ፡፡
አየር መንገዱ የባለፉት 3 ተከታታይ ዓመታት አሸናፊም ነው፡፡
በተመሳሳይም አየር መንገዱ አባል የሆነበት ስታር አሊያንስ ቡድንም “የ2020 ምርጥ የአየር መንገዶች ህብረት” ሽልማትን ለመቀዳጀት በቅቷል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢትሃድ አየር መንገድ በዓለም ምርጥ አየር መንገድነት ሲመረጥ ዱባይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያም የዓለም ምርጥ አየር ማረፊያነት ክብርን ተቀዳጅቷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀናት በፊት የ“Decade of Airline Excellence Award” ሽልማትን መቀዳጀቱ ይታወሳል።
ሽልማቱ አየር መንገዶች ፈታኝ አለም አቀፋዊ ቀውስ በሚያጋጥምበት ወቅት ለሚያሳዩት አፈጻጸም እና ለሚያስመዘግቡት ስኬት የሚሰጥ ነው፡፡