የአፍሪካ ህብረት እየተባባሰ ያለው የሊቢያ ሁኔታ ያሳስበኛል አለ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት በሊቢያ እየተባባሰ ያለው ሁኔታ የሊቢያን ሕዝብ እያሰቃየ መሆኑ በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡
በሊቢያ ላይ የሚስተዋለው የፖለቲካዊና ወታደራዊ ጣልቃገብነት በሀገሪቱ ዉስጥ የበለጠ መፋጠጥን የሚያመጣ ነው ብለዋል ሊቀመንበሩ፡፡
ሊቀመንበሩ የውጭ ኃይሎች ጣልቃገብነት የሊቢያ ህዝብ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት ካለው መሻት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት በሊቢያ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ መፍትሄ እንዲመጣ በቁርጠኝነት ይሰራል ያሉት ሊቀመንበሩ የማህበራዊና የፖለቲካዊ ሚና ያላቸው ኃይሎችም መሪ ሚና መጫወት አለባቸው ብላዋል፡፡
ሊቀመንበሩ አለምአቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካ በሊቢያ ያለው ችግር ወደ ከፋ ደረጃ ደርሶ የሀገሪቱን፣ የቀጠናውንና የአህጉሪቱን ሰላም ወደ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ከመክተቱ በፊት ከአፍሪካ ጎን እንዲቆሙ ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታትም እንደ አፍሪካ ህብረት ሁሉ የሊቢያ ጉዳይ እንደሚያሳስበው አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሊቢያ አሁን ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ መጠየቃቸውን ኒዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
በምክትል ቃል አቀባያቸው በኩል ባቀረቡት ጥሪ በሊቢያ በድጋሚ ተኩስ መቆም አለበት፤ ፖለቲካዊ ውይይትም መጀመር አለበት ብለዋል፡፡
ሊቢያ ለ42 አመታት የመሯት ሙአማር ጋዳፊ ከስልጣን መወገድ በኋላ በተባበሩት መንግስታት እውቅና ያለው ቡድን በአንድ ወገን፣ እውቅና የሌለውን በጄነራል ከሊፋ ሀፍታር የሚመራው ቡድን በተቃራኒ ወገን ሆነው የጀመሩት ጦርነት እስካሁን እንደቀጠለ ነው፡፡
ቱርክ በሊቢያ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ያስፈልጋል በማለት ወታደር ለመላክ ስትወስን፤ ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ጣልቃገብነቱ በሀገሪቱ ያለውን የእርስበእርስ ፍጥጫ ያባብሳል፤ መፍትሄም አያመጣም በማለት የቱርክን እርምጃ አውግዘዋል፡፡