ግጭትና ጦርነትን በማስቀረት ምቹ የልማት ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ተወያይቷል
የህብረቱ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ተጠናቋል
ለባለፉት 2 ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው 36ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ተጠናቋል፡፡
በአባል ሃገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሲካሄድ የነበረው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባው ህብረቱ ያስቀመጠውን ጭብጥ ሃሳቦች ታሳቢ አድርጎ በአህጉሪቱ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ደህንነት ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡
የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ሪፖርትን አድምጦም በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በዝግ ተወያይቷል።
በተለይም ግጭትና ጦርነትን በማስቀረት ልማትን ማምጣት እና የአህጉሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ማቀላጠፍ ስለሚቻልበት ሁኔታ ላይ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡
በተጨማሪም ህብረቱ እያከናወናቸው ያሉ የማሻሻያ ስራዎች፣ የአፍሪካ ህብረት የፋይናንስ ሁኔታ፣ የአፍሪካ ህብረት የመዋቅር ማስተካከል ስራዎችና የህብረቱ አባል አገሮች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላቸውን ተሰሚነትና ተሳትፏቸውን ማሳደግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የትብብር ስራዎች የሁለት ቀናት የውይይት አጀንዳዎች ነበሩ።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የቀረቡለትን ረቂቅ አጀንዳዎችና የውሳኔ ሃሳቦች መርምሮ የገመገመ ሲሆን የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ያቀርባል።
የህብረቱን አዳዲስ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሃገራት በመምረጥም ነው ስራ አስፈጻሚው ትናንት ምሽት ስብሰባውን ያጠናቀቀው፡፡
ኢትዮጵያ እና ጅቡቲን ጨምሮ ካሜሩን፣ቻድ፣ግብጽ፣ማላዊ፣ሞዛምቢክ፣ቤኒን፣ጋና እና ሴኔጋል በምክር ቤቱ አባልነት መመረጣቸው የሚታወስ ነው፡፡