ከተዘጋ 4 ወራትን ያስቆጠረው አይካ አዲስ አሁንም ለሰራተኞቹ ደሞዝ እየከፈለ ነው
ዓለም ገና ከተማ የሚገኘው አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በእዳ ምክንያት ከተዘጋ 4 ወራትን ቢያስቆጥርም አሁንም ከ4 ሺ 5 መቶ ለሚልቁ ሰራተኞቹ ደሞዝ እየከፈለ ነው ተብሏል፡፡
ድርጅቱ በተጠቀሱት ወራት ውስጥ 40 ሚሊዮን ብር ለሰራተኞቹ መክፈሉንም ነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ የባንኩን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ ላደረጉት የተወካዮች ም/ቤት አባላት የገለጹት፡፡
በ3 የድርጅቱ መጋዘኖች የተከማቹና ያለቀላቸው ምርቶች አሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ የሚፈቅድ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡
ከ12 ዓመታት በፊት በቱርክ ባለሀብቶች የተመሰረተው አይካ አዲስ በደረሰበት ኪሳራ እና ባለሀብቱ ጥለውት በመሄዳቸው ምክንያት መዘጋቱን ተከትሎ አበዳሪው ልማት ባንክ ከነሰራተኞቹ ተረክቦ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው፡፡መረጃው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡