ባይደን ለኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር መረጡ
ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ረጅም ልምድ ያላቸውን ኢርቪን ጆሴ ማሲጋ ነው በእጩነት ያቀረቡት
አዲሱ ሹመት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት መለሳለስ መጀመር ያሳያል ተብሏል
አሜሪካ ለኢትዮጵያ አዲስ አምባሳደር ለመሾም መዘጋጀቷ ተነግሯል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ ያገለገሉትን ኢርቪን ጆሴ ማሲጋ ለአምባሳደርነት በእጩነት ማቅረባቸው ነው የተገለጸው።
ኮንግረንሱ ሹመቱን ካጸደቀው ማሲጋ ለአንድ አመት ያህል ክፍት ሆኖ የቆየውን ስልጣን ይይዛሉ ብሏል የኬንያው ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ጌታ ፓሲ በጥር ወር 2022 አንድ አመት እንኳን ሳያገለግሉ መነሳታቸው ይታወሳል።
አሁን ላይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ያሏት ጉዳይ አስፈጻሚ ትሬሲ ጃኮብሰንም የሙሉ አምባሳደርነት ስልጣን ያላቸው አይደሉም።
አሜሪካ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከፌደራሉ መንግስት ጋር ግንኙነቷ ሻክሮ ቆይቷል።
በጦርነቱ ወቅትም ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ስትወተውት የቆየች ሲሆን ኢትዮጵያ ምርቶቿን ወደ አሜርካ ገበያ ያለቀረጥ ከምታስገባበት የአጎዋ ተጠቃሚነት ውጭ ማድረጓም አይዘነጋም።
ከሁለት ወራት በፊት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ከመደረሱ በፊት አፍሪካ ህብረት መሩን ድርድር ስትደግፍ መቆየቷን የምታነሳው ዋሽንግተን፥ ከስምምነቱ ማግስት ከአዲስ አበባ ጋር ግንኙነቷን ማደስ ጀምራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በታህሳስ ወር 2022 ወደ ዋሽንግተን በማቅናት ከአሜሪካ አፍሪካ ጉባኤ ጎን ለጎል ከዋይትሀውስ ሹማምንት ጋር ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የመረጣቸው አዲስ አምባሳደርም ከአንድ አመት በላይ ክፍት የነበረውን የስራ ቦታ የሚደፍንና የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ የሚያሻሽል እንደሚሆን ይታመናል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ኢርቪን ጆሴ ማሲጋ ሹመት ግን በኮንግረንሱ መጽደቅ ይኖርበታል።
በሱዳን እና ጊኒ የአሜሪካ ተልዕኮ ረዳት ሃላፊ የነበሩት ማሲጋ፥ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የደቡብና መካከለኛው እስያ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ተገልጿል።