የፖሊስ መኮንኑ በብጥብጡ ምንም አይነት ጉዳት ባይደርስበትም ሁነቱ ለህልፈቱ ሚና ተጫውቷል በሚል ነው ክሱ የቀረበው
በአሜሪካ በካፒቶል ሁከት የሞተ ፖሊስ ቤተሰቦች 10 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈላቸው ከሰሱ።
በፈረንጆቹ ጥር ስድስት፤ 2021 በተፈጠረው ብጥብጥ ምክንያት የሞተው የካፒቶል ፖሊስ አባል ቤተሰቦች የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በግፍ እንዲሞት” አድርገዋል በሚል ክስ መስርተዋል።
ክሱ ዋሽንግተን በሚገኘው ፍርድ ቤት የተመሰረተ ሲሆን፤ በሁከቱ ማግስት በደም ስትሮክ ምክንያት በ42 ዓመቱ የሞተውን የፖሊስ መኮንን ብሪያን ሲክኒክን በመወከል ትራምፕ ላይ ቀርቧል።
የፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ውጤት በሚረጋገጥበት ካፒቶል ላይ በተፈጸመው ጥቃት የፖሊስ ባልደረባው ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰበት የህክምና መርማሪዎች ጠቅሰው፤ ሞቱ በተፈጥሮ ምክንያቶች እንደሆነ ተናግረዋል።
ሆኖም በጥር ስድስት ላይ የተከሰቱት የሁከት ክስተቶች ለህልፈቱ ወሳኝ ሚና ሳይኖራቸው አይቀርምም ብለዋል ።
"ተከሳሽ ትራምፕ ሆን ብለው ህዝቡን በማስቆጣት በአሜሪካ ካፒቶል እና የሚቃወሟቸውን እንዲያጠቁ መመሪያ ሰጥተዋል፤ አበረታቷል" ብሏል ክሱ።
"በመኮንኑ ላይ የደረሰው ጉዳት እና የእሱን ሞት ጨምሮ የተከሰቱት ብጥብጥ ያስከተለው ጉዳት በተከሳሽ ትራምፕ ንግግር እና ባህሪ ምክንያትና ሊታዩ የሚችሉ ውጤቶች ነበሩ" ሲል ክሱ ገልጿል።
የትራምፕ ቃል አቀባይ አስተያየት ለመስጠት አለመቻላቸውን ሮይተርስ ዘግባል።
ትራምፕ ከ “ስህተት ሞት” በተጨማሪ የፖሊሱን ህዝባዊ መብቶች በመጣስ ጥቃት እና ቸልተኝነትን አድርሰዋል በሚል ተከሰዋል።
ቤተሰቦቹ 10 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጠይቀዋል።
በክሱ ከትራምፕ በተጨማሪ ሁለት በጥር 6ቱ የተሳተፉ ተቃዋሚዎችም ስማቸው ተካቷል ተብሏል።