ቻይና ሰራሹ ቲክቶክ ኩባንያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመራጭ መሆን ችሏል
ቲክቶክ በአሜሪካ መንግስታዊ ተቋማት ጥቅም ላይ እንዳይውል ታገደ።
በፈረንጆቹ 2016 ላይ በቻይና የተሰራው ቲክቶክ የማህበራዊ ትስስር ገጽ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል።
ይህ መተግበሪያ አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በአጭር ጊዜ ለብዙዎች እንዲደርስ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን ለብዙዎችም የገቢ ምንጭ ሆኗል።
ይህ ፈጣን መተግበሪያ በቻይና መሰራቱን ተከትሎ ምዕራባዊያን ሀገራት በጥርጣሬ የሚያዩት ሲሆን በተለይም አሜሪካ በዚህ መተግበሪያ ላይ እምነት እንደሌላት ስትናገር ቆይታለች።
ቻይና ቲክቶክ መተግበሪያን ምዕራባዊያንን ለመሰለል ትጠቀምበታለች በሚል በተደጋጋሚ ክስ ስታሰማ ቆይታለች።
አሁን ደግሞ ይህ መተግበሪያ በአሜሪካ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል ማገዷን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት 19 የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት እና ሰራተኞቻቸው እንዳይጠቀሙ እገዳ አስተላልፈዋል።
ቲክቶክ ኩባንያ በበኩሉ የአሜሪካ ውሳኔ ፖለቲካዊ እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት እንደሌሉ እገዳውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቲክቶክ አክሎም መተግበሪው በደንበኞች ያለው ተቀባይነት እያየለ መምጣቱ ለአሜሪካ ኩባንያዎች ፈተና ስለሆነ እገዳው ሊጣልበት እንደቻለም አስታውቋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባንድ ወቅት ቲክቶክ ኩባንያ ለአሜሪካዊያን እንዲሸጥ መጠየቃቸው ይታወሳል።