የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ100 ሺህ ዶላር ሊያልፍ እንደሚችል ባለሙያዎች እየተነበዩ ናቸው
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ የ10 ሺህ ዶላር ጭማሪ አሳየ፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ዋጋው አሽቆልቁሎ የነበረው የዓለም ምናባዊ ወይም ክሊፕቶከረንሲ መገበያያ ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ በመሳየት ላይ ይገኛል።
ከሰባት ቀናት በፊት አንድ ቢትኮይን በ59 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በ10 ሺህ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡
እንደ ፎርብስ ዘገባ ከሆነ ቢትኮይን በታሪክ ትልቁ የዶላር ምንዛሬው 68 ሺህ 789 ዶላር የነበረ ሲሆን ይህም በሕዳር 2021 ላይ እንደነበር ተገልጿል፡፡
አሁን ለይ አንድ ቢትኮይን በ69 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት እየጨመረ እንደሚሄድ እና እስከ ሚያዚያ ወር ድረስ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ወደ 98 ሺህ ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችል ባለሙያዎች ገምተዋል፡፡
ቢትኮይን ... መንግስታት ምስጢራዊነትን ለምን ይጠላሉ?
የቢትኮይን ዋጋ በተከታታይ ጭማሪ ያሳየው አሜሪካ በምናባዊ መገበያያ ገንዘብ ተቋማት ላይ ስታካሂደው የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቋን ካሳወቀች በኋል ነው ተብሏል፡፡
በተለይም ሀገሪቱ በድጅታል መገበያያ ገንዘቦች አማካኝነት አክስዮን መሸጥ እና መግዛት እንደሚቻል ከፈቀደች በኋላ ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በሺዎች ጭማሪ አሳይቷል።
የምናባዊ ግብይት ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ ሲሆን በዓለማችን በየቀኑ በአማካኝ 90 ቢሊዮን ዶላር በምናባዊ ገንዘቦች ግብይት በመፈጸም ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በዓለማችን ቀዳሚ የሆነው የምናባዊ መገበያያ ገንዘብ ቢትኮይን የተሰኘው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ከ12 ዓመት በፊት ሲሆን የአንዱ ቢትኮይን ዋጋም 12 ዶላር ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ማንኛውንም ምናባዊ መገበያያ ገንዘብ በይፋ ያገደች ሲሆን ለዚህ ግብይት የሚረዱ መሰረተ ልማት አልሚ ኩባንያዎች ግን ወደ ስራ እንዲገቡ ፈቃድ በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡
እስካሁን በተደረገው ጥረትም 25 የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንደወሰዱም ተገልጿል፡፡