ኢትዮጵያ ሁሉንም የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ማገዷ ይታወሳል
የአንድ ቢትኮይን ዋጋ በ100 ሺህ ዶላር ሊመዘር እንደሚችል ተገለጸ፡፡
በፈረንጆቹ 2009 ላይ ጃፓናዊው ሶታሺ ናካሞቶ እንደተፈጠረ የሚታመነው ቢቲኮይን የተሰኘው የድጅታል መገበያያ ገንዘብ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ይህ መገበያያ ገንዘብ ዋጋው በየጊዜው ከፍ እና ዝቅ ሲል የቆየ ሲሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ዋጋው ዝቅተኛ ምንዛሬን አስመዝግቦ ነበር።
ይሁንና በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት እያጋጠመ ባለው የዋጋ ግሽበት እና ሌሎች የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት የቢትኮይን ዋጋ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉ ተገልጿል።
እንደ ሲኤንቢሲ ዘገባ ከሆነ የዓለም ምናባዊ ወይም ክሊፕቶከረንሲ መገበያያ ገንዘብ ከዓመታት በኋላ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
በዚህ ምክንያት አሁን ላይ አንድ ቢትኮይን በ44 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ሲሆን ይህም ከዓመታት በኋላ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።
የቢትኮይን ዋጋ ጭማሪ ያሳየው አሜሪካ ከዓመታት ምርመራ በኋላ በምናባዊ መገበያያ ገንዘብ አክስዮን መሸጥ እና መግዛት እንደሚቻል ከፈቀደች በኋላ ነው።
የቢትኮይን ዋጋ ጭማሪ ካሳለፍነው ወር ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ጭማሪ አድርጓል የተባለ ሲሆን ካለፈው ጥር ወር ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ150 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተገልጿል።
ከሁለት ዓመት በፊት የምናባዊ ወይም ክሪፕዮከረንሲ ግብይቶች ተፈላጊነታቸው መጨመሩን ተከትሎ እስከ 60 ሺህ ዶላር በመመንዘር ላይ ደርሰው ነበር።
የምናባዊ ገንዘብ ተቀባይነት በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት እየጨመረ ቢመጣም እንደ ቻይና ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ግን እገዳ ጥለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለም በአሜሪካ ያሉ የምናባዊ ግብይት ተቋማት ላይ ምርመራ መጀመሩ እና እንደ ሲልከን ቫሊ አይነት ባንኮች ኪሳራ ላይ መውደቃቸው የምናባዊ ግብይት ፍላጎት እያሽቆለቆለ እንዲመጣ ያደረጉ ምክንያቶች ነበሩ።
በነዚህ ምክንያቶችም አንድ ቢትኮይን ከዚህ በፊት ከነበረበት 60 ሺህ ዶላር እስከ 10 ሺህ ዶላር እና በታች ሲመነዘር ቆይቷል።
ኢትዮጵያ ቢትኮይንን መሰል የዲጂታል መገበያያ ገንዘቦችን አገደች
እንደዘገባው ከሆነ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ቢትኮይን ተፈላጊነቱ በታሪክ ከፍተኛ ይሆናል የተባለ ሲሆን አንድ ቢትኮይን እስከ 100 ሺህ ድረስ መመንዘር ይጀምራል፡፡
ከዚህ በፊት በቢትኮይን ግብይት ላይ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የወሉ ሰዎች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው እስከ 100 ዓመት እስር ሊተላለፍባቸው እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎ የምናባዊ ግብይት ላይ ግልጽ ቁጥጥር እና ክትትል መዘርጋቱን ተከትሎ የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ላይ ፍላጎት እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት የምናባዊ ግብይት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ እገዳ መጣሉ አይዘነጋም።
ባንኩ አክሎም ምናባዊ ግብይት ያልተፈቀደ እና ህገወጥ መሆኑን ጠቅሶ የዚህ ግብይት ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም አሰራሩ ስለሚዘረጋበት ሁኔታ በቀጣይ ዝግጅት እንደሚደረግ አስታውቆም ነበር።