በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ቦልሴናሮ እና ዋነኛ ተፎካካሪያቸው ሉላ ዳ ሲልቫ የመራጮችን ትኩረት ስበዋል
ብራዚላዊያን ለቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት የሚመራቸውን ፕሬዝዳንት እየመረጡ ነው፡፡
በ214 ሚሊዮን ህዝብ ብዘት የዓለማችን አምስተኛዋ ባለብዙ ህዝብ ሀገር ብራዚል ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዋን ማካሄድ ጀምራለች፡፡
በዚህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ 11 እጩ ተወዳዳሪዎች ያሉ ቢሆንም የምርጫው ፉክክር ግን አሁን በስልጣን ላይ ባሉት ጄር ፕሬዝዳንት ቦልሴናሮ እና ብራዚልን ከፈረንጆቹ 2003 እስከ 2010 ውስጥ በፕሬዝዳንትነት የመሩት ሉላ ዳ ሲልቫ መካከል ነው፡፡
150 ሚሊዮን ብራዚላዊያን መራጮች በሚሳተፉበት በዚህ ምርጫ ላይ የ76 ዓመቱ ከድሃ ቤተሰብ የተገኙት ሉላ ዳ ሲልቫ ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ቅድመ ግምቶች እየወጡ ይገኛሉ፡፡
በብራዚል በተለይም ድሃ እንደሆኑ በሚነገርላቸው ጥቁር ብራዚሊያዊያን እና ኢኮኖሚውን በያዙት ነጮጭ ብራዚላዊያን መካከል የፖለቲካ ልዩነት አለ፡፡
በዚህ ምርጫ ላይም የቀድሞው የብራዚል ወታደራዊ አመራር የነበሩት እና ላለፉት ሰባት ዓመታት ብራዚልን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ጄር ቦልሴናሮ ከነጭ ብራዚላዊያን እና ሀብታሞች በኩል ጥሩ ድጋፍ እንዳላቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና ፕሬዝዳንት ቦልሴናሮ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የብራዚልን መልካም ስም የሚያጠለሹ ስራዎችን እንደሰሩ እንዲሁም ለኮሮና ቫይረስ መከላከል የሰጡት ምላሽ እና ብራዚል የኢኮኖሚ መድቀቅ እንዲገጥማት አድርገዋል በሚል ትችቶችን እያስተናገዱ ነው፡፡
የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት የነበሩት እና የአሁኑ ዋነኛ ተፎካካሪ ሉላ ዳ ሲልቫ ከ2003 እስከ 2010 ባሉት ሰባት ዓመታት የስልጣን ጊዜያቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብራዚላዊያንን ከድህነት በማውጣት ወደ መካከከለኛ ኢኮኖሚ እንዲገቡ ማድረጋቸው በስኬት እየተነሳላቸው ይገኛል፡፡
ምርጫው በዛሬው ዕለት የሚካሄድ ሲሆን አብላጫ ድምጽ ያገኘው እጩ የመራጮችን 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ድምጽ ካላገኘ ከአንድ ወር በኋላ በሁለት እጩዎች መካከል ዳግም ምርጫ እንደሚካሄድ የሐገሪቱ የምርጫ ህግ ያስረዳል፡፡
በብራዚል በህዝብ የተመረጠ ፕሬዝዳንት የስልጣን ጊዜ ሰባት ዓመታት ሲሆን ከሁለት የምርጫ ጊዜ በላይ ግን በስልጣን ላይ መቆየት አይቻልም፡፡