የስታዲየሙ መጠሪያ ተግባራዊ እንዲሆን የሪዮ ዴጄንሮ ከተማ አስተዳዳሪ እስኪያጸድቁት ይጠበቃል
ብራዚል ጉዙፉን ማራካኛ ስታዲየምን በብራዚላዊው እውቁ የእግር ኳስ ተጨዋች ፔሌ ስም ልትሰይም ነው።
የግዙፉ ማራካኛ ስታዲየም ስም እንዲቀየር የሪዮ ዴጄንሮ ከተማ አስተዳዳሪዎች ድምጽ የሰጡ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት የስታዲየም መጠሪያ “ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ ሬይ ፔሌ” በሚል የሚሰየም ይሆናል።
“ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ” የ80 ዓመቱ እውቁ የእግር ኳስ ተጫዋች ፔሌ ሙሉ መጠሪያ ሲሆን፤ “ሬይ”የሚለው ደግሞ በፖርቹጋል ቋንቋ ንጉስ ማለት እንደሆነም የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
የስታዲየሙ መጠሪያ ተግባራዊ እንዲሆን የሪዮ ዴጄንሮ ከተማ አስተዳዳሪ እስኪያጸድቁት እየተጠበቀ ይገኛል።
ፔሌ ከብራዚል ጋር 3 የዓለም ዋንጫዎችን ያነሳ ሲሆን፤ ለብራዚል በተሳተፈባቸው 91 ጨዋታዎች 77 ጎሎችን ያስቆጠረ ተጫዋች ነበር።በዓለም ክብረ ወሰን የተመዘገበለት 1ሺህ 281 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን በ21 ዓመት የተጨዋችነት ዘመኑ 1ሺህ 363 ጊዜ በጨዋታ ላይ ተሳትፏል።