ቻድ ሩሲያን አስጠነቀቀች
በግንቦት ወር ከሴንትራል አፍሪካ ድንበር አቅራቢያ በመሆን ቻድ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በሩሲያውያን የተደገፈ መሆኑንም ገልፃለች
ከፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ግድያ ጀርባ የሩሲያው ዋግነር ቡድን እንዳለ ማስረጃ አለኝ ብላች
ቻድ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነትን አስመልክቶ ሩሲያን ማስጠንቀቋ ተሰምቷል።
የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሸሪፍ መሃመት ዝነ “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣ የውጭ ጣልቃ ገብነት በሀገሪቱ ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል” ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስለ ሩሲያው “ዋግነር” ቡድን ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው ይህንን ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ የቻድን ደህንነት ለመጠበቅ ሀገሪቱ ማንኛውንም አይነት እርምጃ ትወስዳለች ሲሉም ለኤ.ኤፍ.ፒ ተናግረዋል።
“በሊቢያ ውስጥ ያሉት የሩሲያ ቅጥረኛ ሀይሎች በሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ውስጥም አሉ” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
የቀድሞ ቻድ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ባለፍነው ዓመት የተገደሉትም የሩሲያው “ዋግነር” ቡድን ባሰለጠናቸው ሀይሎች እንደሆነም አስታውቀዋል።
“ቅጥረኛ ሀይሎች መኖራቸው የሚያሳስበን በምክንያት ነው” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሸሪፍ መሃመት ዝነ፤ ቅጥረኞቹ ቻድ ውስጥ ስለመኖራቸው ግን ማረጋገጫ አልሰጡም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም ባሳለፍነው ግንቦት ወር ከሴንትራል አፍሪካ ድንበር አቅራቢያ በመሆን ቻድ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በሩሲያውያን የተደገፈ ነው ብለዋል።
ቻድ በሊቢያ እና በሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ሀይሎች ከሩሲያው ዋግነር ቡድን ጋር የሚያደርጉትን የስልክ ልውውጥ ላይ መድረሱንም ገልፀዋል።
ሞሶኮ በበኩሏ ወታደራዊ አስልጣኞችን ወደ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ መላኳን አምናለች፤ ሆኖም ሀይሎቹ በውጊያ ውስጥ አልተሳተፉም ስትል የሚደርስባትን ውንጀላ አጣጥላለች።