ታሊባን በአሽራፍ ጋኒ የሚመራውን መንግስት በኃይል በማስወገድ ቤተ መንገስት መግባቱ ይታወሳል
የራሺያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ከአፍጋኒስታኑ ከታሊባን መንግስት ጋር መስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ።
በአሸባሪነት ተፈርጆ የነበረው ታሊባን አሜሪካ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ማስወጣቷን ተከትሎ አጭር ጊዜ ውስጥ አፍጋኒስታንን ተቆጣጥሮ ከ20 አመታት በኋላ ቤተመንግስት መግባት ችላል፡፡
ፕሬዘዳንት ፑቲን ይሄንን ያሉት በሩሲያ-ቻይና የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባተኮረው የሻንጋት ትብብር መድረክ በበይነ መረብ በተካሄደበት ወቅት ላይ ነው።
ፑቲን በዚህ ጊዜ እንዳሉት ሩሲያ አፍጋኒስታንን እየመራ ካለው ታሊባን ጋር በጋራ መስራት እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ምእራባውያ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ኢምባሲዎቻቸውን በመዝጋት ዲፕሎማቶቻቸውን በጥፊያ ሲያስወጡ፤ ሩሲያና ቻይና ግን ኢምባሲያቸውም አልዘጉም፤ዲፕሎማቶቻቸውንም አላስወጡም ነበር፡፡
አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት አፍጋኒስታን በውጭ ሀገራት ያላትን መጠባበቂያ ገንዘብ ለማዘጋት እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ ሩሲያ እንደምትቃወምም ፕሬዘዳንት ፑቲን ተናግረዋል።
አሜሪካንን ጨምሮ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ኔቶ አባል ሀገራት ታሊባንን ለመውጋት ከ20 ዓመት በፊት የገቡበት ጉዳይ በሽንፈት ተጠናቆ ሀገራቱ በጥድፊያ ካቡልን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።
ታሊባንም አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ አሜሪካ በአፍጋኒስታን ያደረገችውን ወታደራዊ ተልዕኮ እንዳላሳካች መናገራቸው አይዘነጋም።
ታሊባን አፍጋኒስታን ከምዕራባውያን ጋር የውጭ ግንኙነት ሥራ እንደምትጀምርም በካቡል ቤተመንግስት ውስጥ ሆነው ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት የምትጀምረው የአፍጋኒስታንን ነጻነት እና እስላማዊ እሴቶችን ከሚጠብቁ ሀገራት ጋር እንደሆነም ነበር በወቅቱ የታሊባን ቃል አቀባይ የገለጸው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት በወቅቱ በአፍጋኒታን ጉዳይ ስብሰባ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህ ሰብሰባ ላይም፤ ታሊባን አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣት ለሚፈልጉ ዜጎች ምቹ የመተላለፊያ ሁኔታ እንዲፈጥር፤ ለሀገሪቱ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲዳረስ፤ የሴቶችንን እና ህጻናትን ጨምሮ ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ሩሲያም ተመድ የደረሰበትን ውሳኔ እንደምትከብር እና ከታሊባን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መስራቷን እንደምትቀጥል ዛሬ በይፋ አስታውቃለች።