"CH-YH1000" ድሮን - የቻይና ወታደራዊ እና ሎጂስቲክ ትራንስፖርት አቢዮት ማሳያ
ቤጂንግ ወታደራዊ ሎጂስቲክ ለማመላለስ የሚውለውን ሰው አልባ አውሮፕላን ሙከራ አጠናቃለች
ግዙፉ ድሮን በአስቸጋሪ ስፍራዎች ሎጂስቲክ በፍጥነት ለማቅረብ ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል
ቻይና የወታደራዊ ሎጂስቲክ ዘርፏን ይበልጥ የሚያቀላጥፍ ድሮኗን ሙከራ አጠናቃለች።
"ሲኤች ዩኤቭ" በተሰኘ ኩባንያ የተሰራውና "CH-YH1000" የሚል ስያሜ የተሰጠው ድሮን በሁቤይ ግዛት ቻንግቺ አውሮፕላን ማረፊያ ነው የተሞከረው።
ድሮኑ የቻይናው ፒኤልኤ በቀጣይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ወታደራዊ ሎጂስቲክስ ለማድረስ የያዘውን እቅድ ለማሳካት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።
ቻይና በሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላኖች (ድሮን) እና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቀዳሚነቷን ለማስጠበቅና ጦሯን ከዘመኑ ጋር ለማወዳጀት እየሰራች ነው።
ከአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ጋር የሚስተካከሉ አምስተኛ ትውልድ የውጊያ ጄቶችንም በቅርቡ ማስተዋወቋ ይታወሳል።
እስከ 1 ሺህ ኪሎግራም የሚመዝን እቃ የመሸከም አቅም ያለው "CH-YH1000" ድሮንም የቤጂንግ ወታደራዊ እና ሎጂስቲክ ትራንስፖርት አቢዮት ማሳያ ተደርጎ እየተነሳ ነው።
የመሸከም አቅም
ግዝፈቱ ከድሮን ይልቅ አነስተኛ አውሮፕላን የሚያሰኘው "CH-YH1000" 1 ሺህ ኪሎግራም ወይም አንድ ቶን የመሸከም አቅም አለው። ይህም ለወታደራዊ ሎጂስቲክና ለአስቸኳይ ድጋፍ ማማላለስ ተመራጭ ሰው አልባ ድሮን ያደርገዋል።
የተልዕኮ የቆይታ ጊዜ
"CH-YH1000" ያለማቋረጥ ለ10 ስአታት መብረር የሚችል መሆኑም በሩቅ ስፍራዎች ለሚካሄዱ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ሎጂስቲክ ለማድረስ ያስችለዋል ተብሏል።
የመጨረሻ የበረራ ከፍታ
የቻይናው አዲስ የትራንስፖርት ድሮን እስከ 8 ሺህ ሜትሮች ከፍታ መብረር ይችላል። ይህም በተለያየ የአየር ንብረትና ከፍታ ተልዕኮዎችን መፈጸም ያስችለዋል።
ሲነሳ እና ሲያርፍ
በአጭር መንደርደሪያ መነሳትና በፍጥነት ማረፍ መቻሉም በአስቸጋሪ መልካምድር ሎጂስቲክ ለማድረስ ተመራጭ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
የመጀመሪያ ሙከራ
"CH-YH1000" ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በዡሃይ በተካሄደው የ2024 የቻይና የአየር ትርኢት ላይ ነው። ከወታደራዊ ሎጂስቲክ ትራንስፖርት ባሻገር ለሲቪል ተግባር መዋል ይችላል መባሉ በወቅቱ ትኩረት ስቦ እንደነበር ግሎባል ታይምስ አስታውሷል።