በድብቅ እየተመረቱ ያሉት ድሮኖች ከ50 እስከ 400 ኪሎ ግራም ክብደት መሸከም የሚችሉ እንደሆኑም ተገልጿል
ሩሲያ በቻይና ሚስጢራዊ የድሮን ማምረቻ ማቋቋሟ ተገለጸ።
ለጥቂት ቀናት በሚል የተጀመረው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኝ ሲሆን በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ እዚህ ደርሷል፡፡
ሩሲያ በቻይና ሚስጢራዊ የድሮን ማምረቻ መገንባቷን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ሩሲያ ከቻይና ጋር በመቀናጀት የረጅም ርቀት ሰው አልባ አውሮፕላን ወይም ድሮን እይመረተች ትገኛለች።
ሁለት የአውሮፓ ስለላ ድርጅቶችን ዋቢ አድርጎ የተሰራው ይህ ዘገባ ቤጂንግ እና ሞስኮ ጂ3 የተሰኘ የረጅም ርቀት ድሮን እየገነቡ ናቸው።
በትብብር እየተገነቡ ናቸው የተባለው ድሮን በሰዓት ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ነው ተብሏል።
እንዲሁም ይህ ድሮን ከ50 ኪሎ ግራም እስከ 400 ኪሎ ግራም ድረስ የሚመዝን እቃዎችን የመሸከም አቅም እንዳለውም ተገልጿል።
ቻይና በሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ላይ ገለልተኛ መሆኗን ያሳወቀች ቢሆንም ምዕራባዊያ ሀገራት ግን ሞስኮን በተለያዩ መንገዶች እየረዳች እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ስለ ሩሲያ ድሮን ማምረቻ ፋብሪካ ጉዳይ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጠ ተገልጿል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባሳለፍነው ሳምንት በፒተርስበርግ ከተማ በሚገኝ የድሮን ማምረቻ ማዕከል ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የሩሲያ ጦር ባሳለፍነው ዓመት 140 ሺህ ድሮኖች መታጠቁን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ፑቲን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ድሮን እንዲመረት ማዘዛቸውም ተገልጿል።
ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን የአየር ላይ ጥቃቶች ለማክሸፍ በሚል ከምዕራባዊን ሀገራት ኤፍ-16 የተሰኘው የውጊያ አውሮፕላን እንዲሰጣት ከጠየቀች በኋላ ሀገራት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አሁን ደግሞ ዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ድጋፍ እንዲደረግላት እና በሩሲያ ምድር ጥቃት ማድረስ እንድትችል ሀገራት ይሁንታ እንዲሰጧት እየጠየቀች ሲሆን የተወሰኑ ሀገራት ሲፈቅዱ የተወሰኑት ደግሞ በመቃወም ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን በበኩላቸው የኔቶ ሀገራት ዩክሬን በረጅም ሚሳኤሎች ሩሲያን እንድታጠቃ ከፈቀዱ የቀጥታ ጦርነት ከኔቶ ጋር ሊጀመር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡