የቻይናዋ የጠፈር መንኮራኩር ሩቅ ከተባለው የጨረቃ ክፍል ናሙና ይዛ መሬት አረፈች
የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ቻይና የስፔስ እና የሳይንስ ማዕከል ለመሆን ለምታደርገው ጥረት የተልእኮው መጠናቀቅ ወሳኝ ነው ብለዋል
የቻይናዋ ቸንጅ-6 መንኮራኩር ቻይናን ከጨረቃ የሩቅ ክፍል ናሙና በማምጣት የመጀመሪያዋ አድርጋታለች
የቻይናዋ የጠፈር መንኮራኩር ሩቅ ከተባለው የጨረቃ ክፍል ናሙና ይዛ መሬት አረፈች።
የቻይናዋ ቸንጅ-6 መንኮራኩር ባለፈው ማክሰኞ እለት በሰሜናዊ የቻይና ግዛት ኢነርሞንጎሊያ ስታርፍ፣ ሀገሪቱን ከጨረቃ የሩቅ ክፍል ናሙና በማምጣት የመጀመሪያዋ አድርጋታለች።
መንኮራኩሯ ባለፈው ወር በሩቁ የጨረቃ ክፍል በተሳካ ሁኔታ ካረፈች በኋላ የሰበሰበችውን ሉናር ሶይል ወይም ናሙና ይዛ በቤጂንግ ሰአት ከቀኑ 8:07 ሰአት ማረፏን ሮይተርስ መንግስታዊዉን ሲሲቪን ጠቅሶ ዘግቧል።
ካፕሱሉ መሬት ካረፈ በኋላ ቡዙም ሳይቆይ የቻይና ብሔራዊ ስፔስ አድሚኒስትሬሽን ኃላፊ ዛንግ ኬጂያን የቸንጅ-6 ተልእኮ በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ቻይና የስፔስ እና የሳይንስ ማዕከል ለመሆን ለምታደርገው ጥረት የተልእኮው መጠናቀቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ቸንጅ-6 መንኮራኩር በደቡባዊቷ የሀይናን ደሴት ከሚገኘው የወንቻንግ ማስወንጨፊያ ማዕከል የተወነጨፈችው ባለፈው የፈረንጆቹ ግንቦት ሶስት ነበር።
ናሙናው ለምርምር በአውሮፕላን ወደ ቤጂንግ መላኩን ዘገባው ጠቅሷል።
መንኮራኩሯ ትስበስበዋለች የተባለው ሁለት ኪሎግራም ክብደት ያለው ናሙና ስለመሰብሰቡ ባይታወቅም፣ ናሙናው በቻይናውያን እና በውጭ ሳይንቲስቶች ጥልቅ ምርመራ ይካሄድበታል ተብሏል።
በቸንድ-5 መንኮራኩር ከጨረቃ የቅርብ ክፍል የተሰበሰበው ናሙና አዲስ ማዕድን እንዲገኝ እና የጨረቃ ጂኦሎጂካል እድሜ በትክክል እንዲገመት በር ከፍቷል።
የቸንጅ-6 ስኬት ከአሜሪካ ጋር በቅርብ ፉክክር ውስጥ ላለው የቻይና ሉናር እና የጠፈር ምርምር ፕሮግራም ወደፊት እንደሚያስፈነጥረው ተገልጿል።
ቻይና ከሩቁ የጨረቃ ክፍል ናሙያ ያመጣችው፣ የሉናር ማዕድን ፍለጋ እና ሚሊታራይዜሽን (በጠፈር ወታራዊ እንቅስቃሴ)የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ እየሆነ ባለበት ወቅት ነው።
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ማዕከል(ናሳ) አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን የቻይና ሉናር ፕሮግራም በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለውን የጠፈር ውድድር ይጨምረዋል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።