ውሳኔው መተላለፉን ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ የቢትኮይን የዋጋ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ በመውረድ ላይ ይገኛል
የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ቢትኮይንን ጨምሮ በሁሉም ዲጂታል ገንዘቦች የሚካሄዱ የንግድ ልውውጦች እና ግብይቶች ህገወጥ ናቸው በማለት የእግድ ውሳኔ ማስተላለፉ ተገልጿል።
ከዲጂታል ገንዘቦች ጋር የተያያዙ ማናቸውም ቢዝነሶች ህገወጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ናቸው ያለው ባንኩ፤ ይህ ያልተማከለ የንግድ ስርዓት የዜጎችን የሃብት ደህንነት አደጋ ውስጥ እየከተተ ነው ማቱን የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ቢቢሲን ጠቅሶ ባወጣው ጽህፍ አስነብቧል።
ቻይና በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የቢትኮይንን ገበያ የሚካሄድባት ሃገር እንደመሆኗ ይህ ውሳኔ በዲጂታል ገንዘብ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ይጠበቃል።
በአውሮፓውያኑ ከ2019 ጀምሮ በዲጂታል ገንዘቦች የሚካሄዱ የንግድ ልውውጦች በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ እንዲካሄዱ ሲያስገድድ የነበረው የቻይና መንግስት በተለይም ባሳለፍነው ግንቦት ወር ቢትኮይን እና ሌሎች ክሪፕቶ ከረንሲዎችን በኦንላይን የሚያካሂዱ ሰዎች ምንም አይነት ጥበቃ እንደማይደረግለቸው ሲያስጠነቅቅ ነበር።
አሁን ላይ በቻይና መንግስት የተላለፈው ውሳኔ ማናቸውንም የዲጂታል ገንዘብ ግብይቶች በሃገሪቱ መፈፀም እንደማይቻል እና ይህን ድርጊት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም አካል ህገወጥ የፋይናንስ አንቅስቃሴ በመፈፀም በሃገሪቱ ህግ በወንጀለ እንዲጠየቅ የሚያደርግ ነው።
በዚህ ውሳኔ ውስጥ ግብይቱን ከሚፈፅሙ አካላት በተጨማሪ የዲጂታል ገንዘብ ግብይቶች የሚካሄድባቸው አለም አቀፍ ድረ-ገፆች ለማንኛውም የቻይና ዜጋ የኦንላይን አገልግሎት ሲሰጡ ከተገኘ በህገወጥ ተግባር ተሳትፈዋል በሚል በወንጀል ይከሰሳሉም ተብሏል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ውሳኔው መተላለፉን ተከትሎ የቢትኮይን የዋጋ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ በመውረድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ እስካሁን በላው ሂደት በሰዓታት ውስጥ ብቻ 2,000 ዶላር እንደቀነሰ ተነግሯል።
ከዚህ በኋላ በሚኖሩት የዲጂታል ገንዘብ ግብይቶች እና አጠቃላይ የብሎክቼን ስርዓት ላይ ይህ የቻይና ውሳኔ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ በአለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና በቢትኮይን ማይኒንግ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ላይም ጭምር ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣም ያስረዳሉ።