የዓለም ትኩረትን የሳበው የቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ ጉባኤ
በጉባኤው ቻይና በዓለም መድረክ ላይ አዲስ ሚና እንዲኖራት ሊያደርጉ የሚችሉ የፖሊሲ ውሳኔዎች ይጠበቃሉ
የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ ጉባኤ ለፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ተጨማሪ የስልጣን ጊዜ እንደሚፈቅድ የሚጠበቅ ይጠበቃል
ቻይናን ባለፉት 73 ዓመታት ያስተዳደረው ኮሚንስት ፓርቲ ዓመታዊ ጉባኤውን ጀምሯል።
በቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው ይህ ጉባኤ ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይ ይጠበቃል።
ጉባኤው ቻይና በዓለም መድረክ ላይ አዲስ ሚና እንዲኖራት ሊያደርጉ የሚችሉ የውጭ ግንኙነት፣ ንግድ እና ወታደራዊ የፖሊሲ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑ ይጠበቃል።
በተለይም ቻይና ከሌሎች ሉዓላዊ ሀገራት ጋር በሚኖራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ከዚህ በፊት በምትከተለው ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ እንደምታደርግ መጠበቁ የዓለም ባለጸጋ ሀገራትን ትኩረት ስቧል።
ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ለሁለት ሰዓት ገደማ በቆየው የፓርቲው ጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ስለ ዜሮ ኮሮና ቫይረስ ፖሊሲ፣ ስለ ታይዋን ጉዳይ፣ ስለ ልጆች ውልደት ምጣኔ ፖሊሲ፣ ስለ ንግድ ፣ አየር ንብረት ለውጥ እና ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ዙሪያ ሰፊ ጊዜ ሰጥተዋል።
ታይዋን የጋዛቴ አንድ አካል ናት የምትለው ቻይና በሀይል ሳይሆን በሰላም እና በሂደት ችግሩን መፍታት እንደምትፈልግ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
የዘንድሮው 20ኛው የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ ጉባኤ ለፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ተጨማሪ የስልጣን ጊዜ እንደሚፈቅድ የሚጠበቅ ሲሆን ፓርቲው ይሄንን ከፈቀደ ቻይናን ለረጅም ጊዜ በመምራት ከማኦ ዜዶንግ ቀጥሎ ሁለተኛው መሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
የ69 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ በቻይና መዲና ቤጂንግ የተወለዱ ሲሆን ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንቱ በኮሚንስት ፓርቲ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በሚያደርጉት ረጅም ሰዓት በሚፈጅ የመክፈቻ ንግግራቸው የሚታወቁ ሲሆን በፈረንጆቹ 2017 ላይ ሶስት ሰዓት ከ30 ደቂቃ የፈጀ ንግግር አድርገው ነበር።