የቻይናና ሩሲያ አዲስ ጥምረት እንደሚያሳስበው የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጉባኤን እየተከታተሉ መሆኑንም የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የቻይናን ተጽዕኖ ለመመከት 300 ቢሊዮን ዶላር መመደባቸውን ገልጸዋል
የቻይና እና ሩሲያ አዲስ ጥምረት እንደሚያሳስበው የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ።
የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮች ጉባኤ በቤልጂየም ብራስልስ እየተካሄደ ሲሆን የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊን ስለ ቻይና እና ሩሲያ ጥምረት ጉዳይ አስተያየት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቷ ከአንድ ወር በፊት የቻይና እና ሩሲያ ፕሬዝዳንቶች ሁለቱ ሀገራት ገደብ የለሽ ትብብር እንደሚያደርጉ መስማማታቸውን ተናግረዋል።
የቻይና እና ሩሲያ አዲስ ጥምረት እንደሚያሳስባቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ ገደብ የለሽ ትብብር የሉዓላዊ ሀገራትን ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል ብለዋል።
በመሆኑም የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች ተባባሪ ሃገራትን ይዘን የተሻለ ዓለም ለመፍጠር እንደሚሰሩም ቮንደር ሊን ተናግረዋል።
በተለይም የቻይናን ተጽዕኖ ለመመከት 300 ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደባቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቷ በህግ የበላይነት እና በጋራ ጥቅም የሚመራ ዓለም እንፈጥራለንም ሲሉ ለአምባሳደሮቹ ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በጀቱ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን በሀይል ልማት፣ በጤና መሰረተ ልማት እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ይውላልም ተብሏል።
ሩሲያ ከዩክሬን በሀይል አራት ግዛቶችን ወደ ራሷ መጠቅለሏን የኮነኑት ቮንደርሊን ድርጊቱ የዓለምን በህግ የመገዛት መርህን የጣሰ እንደሆንም አክለዋል
እንዲሁም ቻይና በቅርቡ እንደምታካሂደው የሚጠበቀው የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጉባኤን እየተከታተሉ መሆኑንም ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል።
ይህ የኮሙኒስት ፓርቲ ጉባኤ ቻይና በቀጣይ ስለሚኖራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አመላካች ውሳኔዎችን እንደሚወስን ይጠበቃል።