በዩክሬን ጉዳይ በተሰበሰበዉ የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ቻይና ድምጸ ተአቅቦ አደረገች
የሩስያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ “የውሳኔ ሃሳብ በመጫን ሩሲያን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም” ሲሉ ተደምጠዋል
አምባሰደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ "አንድም ሀገር ከሩሲያ ጋር በድምጽ አልወገነም….አንድም ቢሆን” ብለዋል
አሜሪካ፤ ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን መጠቅለሏን ተከትሎ የጸጥታው ም/ቤት "ህገ-ወጥ" ነው ለተባለው ህዝበ ውሳኔ እውቅና እንዳይሰጥና ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን ምድር እንድታስወጣ የሚያስገድድ የውሳኔ ሃሳብ አቅርባለች፡፡
በተመድ የአሜሪካ ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድና በአልባኒያ ትብብር ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ አስር ሀገራት ሲደግፉት ሩሲያ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገዋለች እንዲሁም የሞስኮ ወዳጅ እንደሆነች የሚነገርላት ቻይና፣ ጋቦን፣ ህንድ እና ብራዚል በድምጸ ተአቅቦ አልፈውታል፡፡
ስብሰባውን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካዋ ተወካይ አምባሰደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ "አንድም ሀገር ከሩሲያ ጋር ድምጽ አልወገነም። አንድም ቢሆን!......ተአቅቦዎቹም ቢሆኑ “በግልጽ ሩሲያን የሚካከሉ አልነበሩም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በስብሰባው የውሳኔ ሃሳቡን በመቃወም የመከራከሪያ ነጥቦች ያቀረቡት በተባበሩት መንግስታት የሩስያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ በበኩላቸው፤ አሜሪካና አጋሮቿ እንደሚሉት ሳይሆን “አሁን በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ያሉት የዩክሬን ክልሎች ከሩሲያ ጋር ለመቀላቀል መርጠዋል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አምባሰደር ኔቤንዚያ ፤ “የዛሬው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ለመጫን በመመኮር ሩሲያን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም”ም ብለዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የዩክሬን አምባሳደር ሰርጊ ኪስሊቴይ በበኩላቸው በውሳኔው ላይ የተስተዋለው ብቸኛው የሩሲያ ተቃውሞ " ከተባበሩት መንግስታት ቻርተር ጀምሮ በጋራ ቃል ኪዳኖቻችን ውስጥ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እውነታውን ለመካድ የሚደረግ ሙከራ መሆኑንና የሩሲያን መገለል ያስመሰከረ ነው" ብለዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የእንግሊዝ ተወካይ ባርባራ ዉድዋርድም እንዲሁ ሩሲያ ህገ-ወጥ ተግባሯን ለመከላከል ቬቶዋን (ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን) አላግባብ ተጠቅማለች ነገር ግን አሁን የዩክሬንን ግዛቶች ለመጠቅለል የሄደችበት ርቀት "ምንም ህጋዊ ተጽዕኖ የለውም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ተወካይዋ የሞስኮ ፍላጎት “ቅዠት ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ቻይና በውሳኔው ላይ ድምጽ ከመስጠት የተቆጠበችው ቻይናም ብትሆን በዩክሬን ስላለው “የተራዘመ እና የተስፋፋ ቀውስ” ያላትን ስጋት ገልጻለች።
በተባበሩት መንግስታት የቤጂንግ አምባሳደር ዣንግ ጁን "የሁሉም ሀገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መጠበቅ አለበት" የሀገራቱ "የደህንነት ስጋቶች" ከግምት መግባባት አለባቸው የሚል መከራከሪያም አሰምተዋል፡፡
ቻይና ፤ ሞስኮ በኪቭ ላይ ጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ስትደግፍ ባትስተዋልም የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ስትተች መቆየቷ አይዘነጋም፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣን እንዳሉት ቻይና ድመጸ ተአቅቦ ለመምረጥ የተገደደችው የሩስያን “አስከፊ ጩኸት” እና የሌሎችን ግዛቶች የግዛት አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል እርምጃ “በማይመች አቋም ውስጥ” እንድትገኝ ስላደረጋት ነው ብለዋል፡፡