እስከ ትናንት ድረስ 4 ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር በተጨባጭ ወጪ ተደርጓል
ቻይና ኮሮናን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታት የሚያስችል የግብር ማሻሻያ አደረገች
ቻይና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል በሚል አዲስ የታክስ ማሻሻያ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡
ማሻሻያው በአንዳንድ ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን ጫና ያቀላል ያለው የሃገሪቱ ፋይናንስ ሚኒስቴር እስከ ትናንት ድረስ 66 ነጥብ 74 ቢሊዬን ዩዋን (9 ነጥብ 56 ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር) በተለያዩ የሃገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ተሰብስቦ እንደነበር አስታውቋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 28 ነጥብ 48 ቢሊዬን ዩዋን (4 ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር) በተጨባጭ ወጪ መደረጉን ምክትል የፋይናንስ ሚኒስትሩ ዩ ዌይፒንግ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም መካከል 17 ነጥብ 09 ቢሊዬን ዩዋን (2 ነጥብ 45 ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር) በሃገሪቱ ማዕከላዊ መንግስት የተመደበ ነው ያለው ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አብዛኛው ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና የሁቤይ ወረርሽኝ ማዕከልን ለመደጎም እንደዋለ ዘግቧል፡፡
ማሻሻያው የወለድ ምጣኔን በግማሽ በመቀነስ እስከ አንድ ነጥብ ስድስት በመቶ በሚደርስ ምጣኔ ከፍተኛ ብድር የሚያቀርቡ ተቋማትን የሚደግፍ ነው፡፡
በትራንስፖርት፣በምግብና መጠጥ አቅርቦት፣በመኝታ እና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት የሚደርስባቸውን ኪሳራ ለማካካስም እስከ 8 ዓመታት በሚደርስ የተራዘመ ጊዜ ግብራቸውን እንዲከፍሉ እንደሚደረግም ምክትል የፋይናንስ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ለህብረተሰብ ጤና ግልጋሎቶች እና ከታች ለሚሰሩ ለወረርሽኝ ቁጥጥር ስራዎች 9 ነጥብ 95 ቢሊዬን ዩዋን (9 ነጥብ 56 ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር) ተመድቧል ያሉም ሲሆን ትራንስፖርትን ጨምሮ መሰረታዊ በሚባሉ ፍላጎቶች ዙሪያ በተሰማሩ የአገልግሎት ተቋማት የሚሰሩ ሰዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ክፍያ ነጻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በወረርሽኝ ቁጥጥሩ የሚሰማሩ ግለሰቦችን ለመደገፍ በሚል ለሚሰጡ ማበረታቻዎች እና ማትጊያዎች አዲስ አማራጭ የግብር ፖሊሲ ይተገበራልም ተብሏል፡፡
አየር መንገዶችን ከኪሳራ ለመታደግ ለሃገሪቱ አቪዬሽን ባለስልጣን የሚከፍሉት ገንዘብ እንዲቀር ተደርጓል፡፡
ማሻሻያዎቹ እ.ኤ.አ ከጥር 1 ቀን 2020 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑ ናቸው፡፡ እስከመቼ የሚለው ግን የቫይረሱ የስርጭት እና ቁጥጥር ሁኔታ እየታየ የሚወሰን ይሆናል፡፡
የቫይረሱ ተጠቂዎች 60 በመቶ የህክምና ወጪ በሃገሪቱ ፋይናንስ ሚኒስቴር የሚሸፈን ነው፡፡ የተለያዩ የድጎማ ድጋፎችንም ያደርጋል፡፡ በግል ለሚያንቀሳቅሱት ቢዝነስ የሚሆን የአንድ አመት የብድር የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ የፊስካል ማሻሻያዎች ተጠቃሚም ይሆናሉ፡፡
የሃገሪቱ የባንክና ኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ኮሚሽንም ለህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች አቅራቢ፣ ክትባትን ለማገኘት የሚያስችሉ ጥናት እና ምርምሮችን ለሚያደርጉ ተቋማት የሚሆን 30 ቢሊዬን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የልዩ ብድርና ወለድ አቅርቦት ማዘጋጀቱንም የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር ዡ ሊያንግ አስታውቀዋል፡፡