ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት የምትስጠው ብድር ከ7 አመታት በኋላ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ቤጂንግ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት 4.6 ቢሊየን ዶላር ብድር ሰጥታለች
የቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት ይደረጋል
ቻና ከ7 አመታት በኋላ ለአፍሪካ ሀገራት የምትሰጠው የተለያዩ አይነት ብድሮች ጭማሪ ማሳየታቸው ተነግሯል፡፡
ከአለም ባንክ እና አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ቀጥሎ የአህጉሪቷ ከፍተኛ አባዳሪ ሆና የቀጠለችው ቤጂንግ 'በአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ፕሮጀክት' በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለአፍሪካ ሀገራት ሰጥታለች፡፡
ኮሮና ከመከሰቱ በፊት በአመት እስከ 10 ቢሊየን ዶላር ድረስ ለአህጉሩ የምታበድረው ቤጂንግ ከወረርሽኙ በኋላ የብድር ፍሰቱ ከግማሽ በታች መቀነሱን የቦስተን ዩኒቨርስቲ ይፋ ያደረገው ጥናት አመላክቷል፡፡
ከኮሮና ሁለንተናዊ ተጽእኖ በመላቀቅ ላይ በሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ቻይና ድጋሚ መሳተፍ መጀመሯ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ ብድሮችን በመሰጠት ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለማጠናከር ከማለም የመነጨ መሆኑን የጥናቱ አጥኚዎች ተናግረዋል፡፡
ከአመታት በኋላ በ2023 በጂንግ የምትሰጠው ብድር ለምን ጨመረ የሚል ጥያቄ ያነሳው የቦስተን ዩኒቨርስቲ ጥናት ሀገሪቷ ለአህጉሩ ባለብዙ ወገን የፋይናንስ ተቋማት የምትሰጠው ብድር ከፍ በማለቱ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡
ይህን ተከትሎም በ2023 4.6 ቢሊየን ዶላር ብድር ስትሰጥ የብድር መጠኑ ከ2022 ከነበረው በሶስት እጥፍ ብልጫ ያለው ነው፡፡
በዚሁ አመት 8 የአፍሪካ ሀገራት እና ሁለት የአፍሪካ ልማት ባንክን የመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማት በርካታ የገንዘብ ብድር ካገኙ መካከል ናቸው፡፡
ቤጂንግ ለሀገራት ከምትሰጠው ብድር ላይ በመቀነስ ለባለብዙ ወገን ድርጅቶች የምትሰጠውን ብድር ብትጨምርም አንጎላ ፣ ግብጽ እና ናይጄሪያ አሁንም የቻይና ከፍተኛ ተበዳሪ ሀገራት መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ምዕራባውያን የእስያዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት አፍሪካውያንን በብድር ወጥመድ እየተበተበች በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተጽእኖ ውስጥ እየከተተች ነው በሚል የሚያነሱትን ተቃውሞ የስትራቴጂ ባለሙያዎች ያጣጥሉታል፡፡
ቻይና በተለይ በታዳሽ ሀይል ግንባታ በጸሀይ ሀይል እና በኤሌክትሪክ ሀይል ግድብ ማመንጫዎች ግንባታ ላይ ለሀገራቱ የሰጠችው ብድር የሚታይ ለውጥን አምጥቷል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
በሲድኒ ዩኒቨርስቲ የምስራቅ እስያ ጉዳዮች ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ላውራን ጆንሰን ከኮሮና በፊት ቻይና ስትሰጥ የነበረው ገንዘብ 10 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ገልጸው በ2023 ሰጥታዋለች የተባለው 4.6 ቢሊየን ዶላር ከኮሮና መከሰት በፊት ከምትሰጠው ገንዘብ ጋር በግማሽ እንኳን እንደማይስተካከል ያነሳሉ፡፡
ይህ የሆነው ደግሞ ለመንገድ ፣ ለባቡር ፕሮጀክት፣ ለኢንዱስትሪዎች እና በአጠቃላይ ለግዙፍ መሰረተ ልማቶች ስትሰጥ የነበረውን ድጋፍ በመቀነሷ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ቤጂንግ አዳዲስ ብድሮችን ከመፍቀድ ይልቅ ቀደም ብለው በብድር የተሰሩ ኢንቨስትመንት እና መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር ብድሯ እንዲመለስላት ትፈልጋለች ነው ያሉት፡፡
በመጪው ሳምንት የቻይና አፍሪካ ትብብር የመሪዎች ፎረም የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ በጂንግ በተለያዩ የትብብር ዘርፎች አዲስ የብድር ማዕቀፍ ይፋ እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡