እስራኤል ከእሁድ የሚጀምር በጋዛ የ3 ቀናት የተኩስ አቁም ልታደርግ ነው
የተኩስ አቁሙ በጋዛ እየጨመረ የመጣውን የፖሊዮ በሽታ ለመከላከል የክትባት ስርጭት እንዲከናወን ነው
የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ በጋዛ የፖሊዮ ክትባት ስርጭት 90 በመቶ ተቋርጧል
እስራኤል ለሶስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷ ተነገረ፡፡
ከመጪው እሁድ ጀምሮ የሚደረገው የተኩስ አቁም በጋዛ የፖሊዮ ክትባትን ለማሰራጨት ከተመድ እና ከአለም ጤና ድርጅት የቀረበላትን ጥሪ እስራኤል መቀበሏን ተከትሎ ነው፡፡
በዌስት ባንክ የአለም ጤና ድርጅት ተወካይ ሪክ ፒፕርኮርን እንደተናገሩት የክትባቱ ስርጭት በማዕከላዊ ፣ በደቡባዊ እና ሰሜናዊ ጋዛ የሚከናወን ሲሆን በመጪዎቹ ሶስት ቀናት የመጀመርያ ዙር ክትባቱን አዳርሶ ለመጨረስ እቅድ ተይዟል፡፡
የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ የክትባቱን ሂደት ለመደገፍ ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የጋዛው ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ አለምአቀፋዊው የፖሊዮ ክትባት በጋዛ 90 በመቶ ተቋርጦ የቆየ ሲሆን በዚህም በሽታው በአዲስ መልክ በበርካታ ህጻናት ላይ መታየቱ ስጋት ፈጥሯል፡፡
በመጀመርያው ዙር የክትባት ሂደት ከ640 ሺህ በላይ እድሜያቸው ከ10 አመት በታች የሆኑ ህጻናትን ለማዳረስ 1.26 ሚሊየን ዶዝ ክትባት ወደ ጋዛ ተጓጉዟል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት ክትባቱን ለመሰጠት ያገኘው ሶስት ቀን በቂ ባይሆንም የመጀርያ ዙር ክትባቱን ለማሰራጨት እና በሽታውን መዛመት ለመቀነስ ጥሩ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም ሁለተኛ ዙር ክትባቱን በአራት ሳምንታት ውስጥ ለማከናወን ተመሳሳይ የተኩስ አቁም ለማድረግ እስራኤል ፈቃደኛ እንደምትሆን ተስፋ እናደርጋለን ብሏል ድርጅቱ፡፡
የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ 90 በመቶ የጋዛ ነዋሪ ከቀየው የተፈናቀለ ሲሆን በተጨማሪም በሰርጡ ከፍተኛ የምግብ ፣ የመጠጥ ውሀ እና መሰረታዊ አገልግሎት ከፍተኛ እጥረት መፈጠሩ ይነገራል፡፡
ፖሊዮ ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት ላይ የሚከሰት እስከሞት የሚያደርስ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡