የቻይና እና የአሜሪካ ስፖርተኞች በአንድ ወገን ሆነው ሊጫወቱ ነው
ሀገራቱ በፖለቲካ ፍጥጫ ላይ ቢሆኑም ስፖርተኞቹ ግን ለተመሳሳይ ዓላማ አብረው ተሰልፈዋል
የቻይናና የአሜሪካ ስፖርተኞች በአንድ ወገን ሆነው የጠረንጴዛ ቴኒስ እንደሚጫወቱ ተነግሯል
በፖለቲካና በኦኮኖሚ የበላይነት ፉክክር ውስጥ የሚገኙት የቻይና እና የአሜሪካ ስፖርተኞች በአንድ ወገን ሆነው የጠረንጴዛ ቴኒስ እንደሚጫወቱ ዓለም አቀፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የሁለቱ ሀገራት ተጫዋቾች፤ በጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የፍጻሜ ውድድር በአንድ ወገን ሆነው ሊጫወቱ ሲሆን፤ ውድድሩም ከነገ ጀምሮ እስከ ፈረንጆቹ ሕዳር 29 ይካሄዳል።
በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ የአሜሪካ እና የቻይና የጠረንጴዛ ቴኒስ ተወዳዳሪዎች በድብልቅ የውድድር አይነት አንድ ላይ ሆነው ይጫወታሉ ተብሏል።
የቻይናዎቹ ሊን ጋኦዩዋን እና ዋንግ ማንዩ ከአሜሪካኖቹ ሊሊ ዣንግ እና ካናክ ጅሃ ጋር ተጣምረው እንደሚጫወቱም ነው ፌዴሬሽኑ ያስታወቀው። ውድድሩ በአሜሪካ የሚካሄድ ሲሆን ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ሆኗል።
ሻምፒዮናው በዚህ ዓመት አምስት ውድድሮችን ያካተተ ሲሆን፤ በወንዶች እና በሴቶች ነጠላ እና በድርብ እንዲሁም ድብልቅ ውድድሮችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
ቻይና 11 የጠረንጴዛ ቴኒስ ተጫዋቾችን ውድድሩ ወደ ሚዘጋጅባት ሂዩስተን ከተማ እንደምትልክ ተገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢን ፒንግ ከሰሞኑ የመጀመሪያውን የበይነ መረብ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በጉጉት ተጠብቆ የነበረው የ ”ኃያላን ሀገራት መሪዎች ” ውይይት በታይዋን፣ ንግድ እና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ መነጋገራቸው ተዘግቧል።