ኢትዮጵያ በስኬትቦርዲንግ ጨዋታ ኦሎምፒክ ላይ እንድትሳተፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የስፖርቱ ተጫዋቾች ይናገራሉ
ስኬት ቦርዲንግ አሁን አሁን በኢትዮጵያ እየተለመደ የመጣ አዲስ ስፖርታዊ ጨዋታ ሆኗል።
ስኬት ቦርዲንግ በአብዛኞች ዘንድ እምብዛም ባይታወቅም፤ ተጫዋቾቹ ግን ስኬት ቦርዲንግ በኢትዮጵያ ከተጀመረ ከ10 ዓመት በላይ አስቆጥሯል ይላሉ።
መስከረም 22፣ 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ከሀዋሳ የመጡ የስኬት ቦርዲንግ አባላት በበዓሉ ላይ የተለያዩ ትርኢቶችን ስያሳዩ ተመልክተናል።
የስኬት ቦርዲንግ ቡድኑ መሪ ጂሚ ካርሎስ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረገው ቆይታ “ሐዋሳ ላይ የመጀመሪያው ስኬተር ነበርኩ” ያለ ሲሆን፤ የስኬት ቦርዲንግ ጨዋታን ሀዋሳ ከተማ ላይ ከጀመረ 16 ዓመታት እንደተቆጠሩ ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 3 የስኬት ቡድኖች አሉ የሚለው ጂሚ፤ የመጀመሪያው አዲስ አበባ ላይ ያለው እና ኢትዮጵያ ስኬት በሚል መጠሪያ የሚታወቅ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሁለተኛው ቡድን እሱ የሚመራው እና ሀዋሳ ስኬት በሚል የሚጠራ ሲሆን፤ ሶስተኛው ቡድን ደግሞ ኮንሶ ውስጥ ይገኛል ብሏል፡፡
የስኬት መጫወቻ ፓርኮችም በመገንባት ላይ መሆኑን የሚያነሳው ጂሚ፤ የመጀመሪያ የስኬት ፓርክ በአዲስ አበባ ሳር ቤት አካባቢ ከ5 ዓመታ በፊት ማትም በ2009 ላይ መገንባቱን ያስታውሳል።
በመቀጠልም ሁለተኛው የስኬት ፓርክ በ2010 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ በሚገኘው የወጣቶች ማእከል እንደተገነባ ያስታወቀ ሲሆን፤ ሶስተኛው የስኬት ፓርክ በኮኖሶ መገንቱን ይናገራል።
ስኬት ቦርዲንግ በአሁኑ ወቅት በኦሎምፒክ ላይ መጫወት የተጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያንም በስኬት ቦርዲንግ በኦሎምፒክ ላይ እንድትሳተፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል፡፡
ሆኖም ግን የስኬት ቦርዲንግ ጨዋታን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ አሁንም በርካታ ፈተናዎች እንዳሉ በመጥቀስ፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ስፖርቱ በመንግስት እጅ አለመግባት ነው ብሏል።
የስኬትቦርድ ሰሌዳዎችን ጨምሮ ሌሎችም ለስፖርቱ የሚጠቅሙ ቁሳቁሶችን ሁላ በበኢትዮጵያ ውስጥ አግኝተን መግዛት አንችልም የሚለው ጂሚ፤ ለስፖርቱ የሚረዱ ቁሳቁሶችን በልመና እና በእርዳታ እያገኙ መሆኑንም ተናግሯል።
ስፖርቱ ኢንዲያድግ በፌዴሬሽን ደረጃ ቢቋቋም መልከም ነው የሚል ሀሳብ ያነሳው ጂሚ፤ የስኬት ቦርድ ስፖርት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያደርግ መንግሰት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።