የአሜሪካ እና የቻይና መሪዎች ለኃያልነት በሚደረግ ትግል ውስጥ “መከባበር” እንዲኖር ተወያዩ
መሪዎቹ ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ በከተቷቸው የንግድ፣ የታይዋን እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል
ጆ ባይደን እና ሺ ጂንፒንግ የአውራነት ፉክክሩ የግጭት ምንጭ እንዳይሆን ማረጋገጥ ይገባናል ብለዋል
የአሜሪካ እና ቻይና መሪዎች ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት ለኃያልነት የሚያደርጉትን ፉክክር በተመለከተ የበይነ መረብ ውይይት አደረጉ፡፡
ለሶስት ሰዓታት በዘለቀው የበይነ መረብ ውይይት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የአውራነት ፉክክሩን የተመለከቱ በርካታ ጉዳዮችን አንስተው መወያየታቸው ተነግሯል፡፡
“አሜሪካ በቻይና ፖሊሲዎቿ ላይ የሰራችውን ስህተት ማረቅ አለባት”-ቻይና
በመካከላቸው ያለው የአውራነት ትንቅንቅ እንዴት ባለ መልኩ ሊመራ እንደሚገባ በማንሳት መወያየታቸውን ያስታወቁት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ ከእርሱ [ሺ ጂንፒንግ] ጋር በቅንነት እና በቀጥታ መነጋገሩ ትንቅንቁ ወደ ግጭት እንደማያመራ ማረጋገጫ ነው” ብለዋል፡፡
ፉክክሩ የግጭት ምንጭ እንዳይሆን ማረጋገጡ “ የእኛ ኃላፊነት ነው” ሲሉ መናገራቸውንም ባይደን አስታውቀዋል፡፡
በፉክክሩ መከባበር እንዲኖር የጠየቁት የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በበኩላቸው በዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ተቀራርበው በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
ቻይና እና አሜሪካ “በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ያልተጠበቀ ስምምነት” አደረጉ
ኮቪድ-19ኝንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመሳሰሉ ፈተናዎች የተቀናጀ ምላሽ የሚሰጥ የተረጋጋ ዓለም አቀፋዊ ድባብን ለመፍጠር የሃገራቱ የተረጋጋ ግንኙነት እንደሚያስፈልግም ነው ሺ የተናገሩት፡፡
ሊከባበሩ፣ ከግጭቶች ታቅበው በሰላም ሊኖሩ እና አሸናፊ ሊያደርጓቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሊተባበሩ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
መሪዎቹ ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ በከተቷቸው የንግድ፣ የታይዋን እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ሆኖም ውይይታቸውን በተመለከተ ከማስታወቅ ውጭ ያደረጉት ስምምነት እንዳለ ያስታወቁበትም ሆነ ያወጡት የጋራ መግለጫ የለም፡፡