ቻይና ከ72 ዓመት በኋላ ዝቅተኛ የመውለድ ምጣኔ አስመዘገበች
በ2020 ዓመት 12 ሚሊዮን ህጻናት ሲወለዱ በ2021 ግን ቁጥሩ ወደ 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቀንሷል
በ2021 ዓመት ከአንድ ሺህ ቻይናዊያን መካከል ልጅ የወለዱት 7 ያህሉ ብቻ ናቸው
ቻይና ከ72 ዓመት በኋላ ዝቅተኛ የመውለድ ምጣኔ አስመዘገበች፡፡
ከዓለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ቻይና በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2021 ዓመት ከ1949 ዓመት ወዲህ ዝቅተኛው ልጅ የተወለደበት ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ቻይና ከ15 ዓመት በፊት የህዝብ ቁጥሩ እድገት መጨመር አሳስቧት ዜጎቿ ከአንድ ልጅ በላይ እንዳይወልዱ የሚከለክል ህግ አውጥታ በመተግበር ላይ ነበረች፡፡
የውልደት ምጣኔው ከሚጠበቀው በላይ መቀነሱ እና የአገሪቱ ኢኮኖሚ በማደጉ ምክንያትም በ2016 ዓመት ፖሊሲዋን በመቀየር ቻይናዊያን እስከ ሁለት ልጅ መውለድ እንዲችሉ ለዜጎቿ ፈቅዳም ነበር፡፡
ይሁንና በተለይም በቻይና ትላልቅ ከተሞች የሚኖሩ ቻይናዊያን የኑሮ ውድነቱ በመጨመሩ ምክንያት ልጅ የመውለድ ምጣኔው እየቀነሰ እንዲሄድ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በከተሞች ውስጥ በእድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር መጨመር ያሳሰባት ቻይና ከአንድ ዓመት በፊት ዜጎቿ እስከ ሶስት ልጅ ድረስ መውለድ እንዲችሉ ፖሊሲ አውጥታም ነበር፡፤
ይሁንና በተጠናቀቀው 2021 ዓመት በቻይና ታሪክ ከ1949 ዓመት በኋላ ዝቅተኛው የውልደት መጠን መመዝገቡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚሁ ዓመት ከአንድ ሺህ ቻይናዊያን ልጅ የወለዱት 7 ያህሉ ብቻ ሲሆኑ እንደ አገር የውልደት ምጣኔው በ72 ዓመት ታሪክ ውስጥ ዝቅተኛው መሆኑን ዘገባው አክሏል፡፡
በቻይና አሁን ላይ የውልደት ምጣኔው ከ1 በመቶ በታች ሲሆን በየዓመቱ የሚወለዱ ህጻናት ቁጥር እና ከስራ ዓለም ከሚገለሉ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ያነሰ መሆኑ ቻይና ዜጎቿ ልጆችን እንዲወልዱ በማበረታታት ላይ ናት፡፡
በፈረንጆቹ 20220 ዓመት 12 ሚሊዮን ህጻናት ሲወለዱ በ2021 ግን ቁጥሩ ወደ 10 ነጥብ 6 አሽቆልቁሏል፡፡
የውልደት ምጣኔውን ለመጨመር ቻይና ወላጆች ልጆች እንዳይወልዱ የሚያደርጉ የኢኮኖሚ ማበረታቻዎችን ለመስጠት ፖሊሲ ያወጣች ሲሆን የትምህርት ቤት ክፍያዎች፣የጡረታ ጊዜ ክፍያዎች እና የኢንቨስትመንት ማበረታቸውችን አድርጋለች፡፡