በዋሽንግተን የቻይና አምባሳደር የነበሩት ኪን ጋንግ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሸሙ
ቻይናን ላለፉት 10 ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርንነት ያገለገሉት ዋንግ ዪ ከሀላለፊነታቸው ተነስተዋል
አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ ጋዜጠኛም ሆነው አገልግለዋል
በዋሸንግተን የቻይና አምባሳደር የነበሩት ኪን ጋንግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሸሙ፡፡
የ56 ዓመቱ ኪን ጋንግ ቻይናን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ መሾማቸውን የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ቻይናን ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ዋንግ ዩ ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ ሲገለጽ በምትካቸውም በዋሸንግተን የቻይና አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት ኪን ጋንግ ተሹመዋል፡፡
የስራ ዘመናቸውን ጋዜጠኛ ሆነው የጀሙት አዲሱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸውን በዲፕሎማትነት ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል ተብሏል፤፤
ኪን ጋንግ ወደ ዋሸንግተን ከመዛወራቸው በፊት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እና በሌሎች ተያያዥ ስራዎች ዙሪያ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ምዕራባዊያንን አምርረው በመተቸት ከሚታወቁ የቻይና ዲፕሎማቶች መካከል አንዱ የሆኑት ጋንግ ሀገራቸው ከአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ጋር የገባችውን መካረር የበለጠ ሊያጎሉት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
አዲሱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፕሬዝዳንት ሺ ዢ ፒንግ አድናቂ ናቸው የሚባልላቸው ሲሆን ቻይና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ጎልታ እንድትሰማ ያደርጋሉም ተብለዋል፡፡
ኪን ጋንግ በቤጂንግ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዩንቨርሲቲ እንደተማሩ ሲገለጽ ካላቸው የስራ ልምድ እና ፍላጎት አንጻር ሀገራቸውን ለረጅም ጊዜ ያገለግላሉ ተበሏል፡፡