አሜሪካ በቀጥታ ጦርነት እንዲጀመር እየተነኮሰች መሆኗን ቻይና አስታውቃለች
አሜሪካ የዓለማችን ቀጥታ ስጋት መሆኗን የቻይና መከላከያ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አሜሪካ ከሰሞኑ አዲስ ወታደራዊ የስትራቴጂክ እቅዷን በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፊርማ ይፋ አድርጋለች።
ይህ አዲስ የአሜሪካ ወታደራዊ እቅድ በእስያ ፣በምስራቅ አውሮፓ፣ በባህረ ሰላጤው እና ሌሎች ሀገራት ላይ ወታደራዊ ትብብሮችን ማስፋት ኢላማው አድርጓል።
ቻይና ይህ የዋሽንግተን ወታደራዊ እቅድ ያሳሰባት ሲሆን እቅዱን አስቀድማ ተቃውማለች። በታይዋን ጉዳይ ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ ያሉት ዋሸንግተን እና ቤጂንግ ወደ ቀጥታ ጦርነት ሊያመሩ እንደሚችሉ ተሰግቷል።
የቻይና መከላከያ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ እንዳለው አሜሪካ የዓለማችን ቀጥታ ስጋት መሆኗን ጠቅሷል።
አሜሪካ በተደጋጋሚ ያደረገቻቸውን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንደተመለከትነው ዋሸንግተን ዓለም እየተመራችበት ያለውን ስርዓት ለማበላሸት እየሞከረች ነውም ብሏል።
አሜሪካ የሀይል የበላይነቷን ለማስቀጠል በቀጥታ ጦርነት ከመጀመር ጀምሮ ግጭቶችን እስከመደገፍ እርምጃ እየወሰደች መሆኗንም ቻይና አስታውቃለች።
በተለይም ዓለማችን ከፍተኛ የሰብዓዊ ጉዳቶችን እያደረሱ ያሉ ግጭቶች እና ጦርነቶች ጀርባ የዋሸንግተን እጆች እንዳሉ ቻይና ጠቁማለች።
አሜሪካ በቻይና የበላይነቷ እንዳይነጠቅ ታይዋንን እና የእስያ ደቡባዊ የባህር ዳርቻዎችን በመጠቀም ከቻይና ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብታለች።
የቻይና የንግድ እና ኢኮኖሚ ፍጥነትን ለመጉዳትም በየጊዜው የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማዕቀቦችን ጥላለች።
ቻይናም በአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን የታይዋን ጉዳይ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ከፋ ደረጃ እያደረሰው ይገኛል።
ሩሲያ በዩክሬን የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ ሞስኮን ከዓለም ለመነጠል በሚል አሜሪካ የወሰደቻቸው የማዕቀብ እርምጃዎች በቻይና ምክንያት የታሰበውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ ይገለጻል።
ሩሲያ እና ቻይና በአውሮፓ እና እስያ እየፈጠሩት ያለው አዲስ ጥምረት ያሳሰባት አሜሪካ ኔቶ ወደ ምስራቅ አውሮፓ እና እስያ እንዲስፋፋ ግፊት በማድረግ ላይ ትገኛለች።