የአየር ንብረት ለውጥ ግጭቶች፣ አደጋዎች እና መፍትሄዎች
የአየር ንብረት አደጋ ከአካባቢያዊ ባሻገር ወደ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ጸጥታ ጉዳዮች የሚዘልቅ ነው
ተመድ የአየር ንብረት ለውጥ የምግብ፣ የውሃ እና የኑሮ እጦትን ሊያባብስ ይችላል ሲል ተናግሯል
የአየር ንብረት አደጋ ተጽዕኖ ከአካባቢያዊ አውድ ባሻገር ወደ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ጸጥታ ጉዳዮች የሚዘልቅ ነው።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ የጸጥታ ስጋቶችን መረዳት እና ምላሽ መስጠት ሀገራት እና ተቋማት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ሆኗል።
የአየር ንብረት ደህንነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እይታ የአየር ንብረት ቀውስ በሰላም እና ደህንነት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በተለይም በደካማ እና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ያለውን ተጽዕኖ ያመለክታል።
ተመድ የአየር ንብረት ለውጥ የምግብ፣ የውሃ እና የኑሮ እጦትን ሊያባብስ ይችላል ሲል ተናግሯል።
ይህ ደግሞ ለተፈጥሮ ሀብት ሽሚያ መጨመር፣ ማህበራዊ አለመረጋጋት እና መፈናቀልን የመሳሰሉ አስከፊ መዘዞች ያስከትላል።
በአንድ ሀገር ወይም ክልል ውስጥ ውጥረቶችን፣ ግጭቶችን እና አለመረጋጋትን ለመጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ፤ ግጭትን ሊያባብስ ወይም ሊያራዝም ይችላል። ይህም ሰላምን ለማግኘት እና ለማስቀጠል አስቸጋሪ ያደርገዋል። ግጭት የአየር ንብረት እርምጃን ሊያስተጓጉል ወይም ሊያደናቅፍ ይችላል።
የአየር ንብረት ደህንነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?
እ.አ.አ. በ2030 የአየር ንብረት ለውጥ እስከ 130 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጨማሪ ሰዎችን ወደ ድህነት ሊገፋ እንደሚችል ተመድ ያትታል።
እነዚህ አስፈሪ ግምቶች የምግብ እና የውሃ እጦት፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደካማነት እና የፖለቲካ ቅሬታዎች ያመራሉ።
ባልተረጋጉ አካባቢዎች እነዚህ ተጽዕኖዎች የደህንነት ፈተናዎችን እና አለመረጋጋትን ሊያባብሱ ይችላሉ።
ከዚህም በላይ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ የጸጥታ አደጋዎች ብዙውን ጊዜ ሴቶችን ባልተመጣጠነ ደረጃ ይጎዳሉ።
ለዚህም ነው የተባበሩት መንግስታት ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰጡ ምላሾች ከግጭት መከላከል እና ሰላም ግንባታ እርምጃዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆን አለባቸው የሚለው።
ለአየር ንብረት እርምጃ ደካማ እና ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ውስጥ ገንዘብ መመደብ ወሳኝ ነው።
ገንዘቡ በአዎንታዊ መልኩ ጥቅም ላይ ከዋለ ትብብርን ለማጠናከር፣ መተማመንን እንደገና ለመገንባት እና ማህበራዊ መዋቅርን ለመጠገን ጠቃሚ እድል ሊሆን ይችላል።