ተዘግቶ የነበረው ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ መከፈቱን እማኞች ገለጹ
ፖሊስ አደጋው ጥር 10 ከምሽቱ 5 ሰአት አካባቢ መከሰቱን ተናግሯል
ዋና ኢንስፔክተሩ በልዩ ዞኑ ተደጋጋሚ ክስተት ስላለ ለዞንና ለክልል ሪፓርት ማድረጋቸውን ገልጸዋል
የሚኒባስ ሹፌር ህይወት ማለፍን ተከትሎ ተዘግቶ የነበረው ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚወስደው ዋና መንገድ አሁን መከፈቱን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ጠዋት በኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞን ህይወቱ ያለፈው ሹፌር ሞት ምክንያት ይጣራ“ፍትህ እንፈልጋለን” ባሉ ወጣቶችና ሹፌሮች በጣርማበር ወረዳ ደብረሲና ከተማ ላይ መንገድ መዘጋቱን እማኞችን አነጋግሮ አል ዐይን አማርኛ ዘግቦ ነበር፡፡
ህይወቱ ያለፈው ሹፌር የቀብር ስነ ስርዓት መፈጸሙን እማኞች ተናግረዋል፡፡
እማኞቹ እንዳሉት መንገዱ ከዛሬ ከጠዋቱ 1፡30 ጀምሮ ዝግ ሆኖ ነበር፤ ከሁለቱም አቅጣጫ የሚመጡ ተሸከርካሪዎች ቆመውም ነበር፡፡
ዛሬ ጠዋት የጣርማበር ወረዳ የፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሽዋታጠቅ ኃ/ስላሴ ክስተቱ የተፈጠረው ጥር 10 ከምሽቱ 5 ሰአት አካባባቢ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ተሽከርካሪ ላይ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ዋና ኢንስፔክተሩ እንደገለጹት የአካባቢው ወጣቶችና ሹፌሮች፣ ሹፌሩ የሞተው በትራፊክ አደጋ ነው ቢባልም “በጥይት ነው” የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸውና ምክንያቱ በትክክል እንዲጣራ ድምጽ አስምተዋል ብለዋል፡፡
በልዩ ዞኑ ተደጋጋሚ ግድያ ስለሚያጋጥም ችግሩን ለዞንና ለክልል ሪፖርት ማድረጋቸውንና ጉዳዩ እንዲጣራ እንደሚደረግ ኢንፔክተሩ ተናግረዋል፡፡