በሹፌር ግድያ ምክንያት በተነሳ ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚወስደው መንግድ ተዘጋ
ፖሊስ አደጋው ጥር 10 ከምሽቱ 5 ሰአት አካባቢ መከሰቱን ተናግሯል
ፖሊስ የሹፌሩ ሞት ትክክለኛ ምክንያት እንዲጣራ ለዞንና ለክልል ሪፖርት ማድረጉን ገልጿል
በአማራ ክልል ኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞን ጨፋ ሮቢ አካባቢ “ኬላ ጥሰኃል” በሚል ምክንያት የሚኒባስ ሹፌር ተገደለ መባሉን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚወስደው ዋና መንገድ ደብረሲና ላይ መዘጋቱን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
በጨፋ ሮቢ የተገደለው ወጣት የአካባቢው ነዋሪ በመሆኑ የአካባቢው ወጣቶች “ፍትህ እንፈልጋለን” በሚል ድምጽ ማሰማታቸውንና መንገድ መዝጋታቸውን እማኞች ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
እንደ እማኞቹ ገለጻ ከሆነ መንገዱ ከዛሬ ከጠዋቱ 1፡30 ጀምሮ ዝግ ሆኗል፤ ከሁለቱም አቅጣጫ የሚመጡ ተሸከርካሪዎች ቆመዋል፡፡
ነገርግን የጣርማበር ወረዳ የፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሽዋታጠቅ ኃ/ስላሴ የመንገዱን መዘጋት ያረጋገጡ ቢሆንም አሁን ላይ ሰልፍ ወጥተው ከነበሩት የከተማው ሹፌሮች ጋር በመነጋር እንቅስቃሴ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ክስተቱ የተፈጠረው ጥር 10 ከምሽቱ 5 ሰአት አካባባቢ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ተሽከርካሪ ላይ መሆኑን ኢንስፔክተሩ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው ጨፋፎቢ ላይ በተገደለው ሹፌር ምክንያት በአካባባቢው ያሉ የሚኒባስና የባጃጅ ሹፌሮች ዘግተውት እንደነበረና ውይይት በማድረግ መንገዱ መከፈቱን ገልጸዋል፡፡
ዋና ኢንስፔክተሩ እንደገለጹት ሹፌሩ የሞተው በትራፊክ አደጋ ነው ቢባልም “በጥይት ነው” የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸውና ምክንያቱ በትክክል እንዲጣራ ድምጽ አስምተዋል ብለዋል፡፡
በልዩ ዞኑ ተደጋጋሚ ግድያ ስለሚያጋጥም ችግሩን ለዞንና ለክልል ሪፖርት ማድረጋቸውንና ጉዳዩ እንዲጣራ እንደሚደረግ ኢንፔክተሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚመለከተውን አካል አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው የአካባቢው የአይን እማኞች መንገዱ እስካሁን ዝግ መሆኑንና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መቆሙን ተናግረዋል፡፡