ዓለም ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ምጣኔ ሃብታዊ ልሽቀት ውስጥ ትገኛለች- የዓለም ባንክ
ኢትዮጵያም ይኸው ችግር ከገጠማቸው ሃገራት መካከል ነች
በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመትም ምጣኔ ሃብቷ በ5 ነጥብ 2 በመቶ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ተገምቷል
ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ምጣኔ ሃብታዊ ልሽቀት ውስጥ ትገኛለች- የዓለም ባንክ
የኮሮና ወረርሽኝ በፈጠረው ጫና ምክንያት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ያለው የዓለም ምጣኔ ሃብት እድገት በ5 ነጥብ 2 በመቶ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ዜጎችን ከቫይረሱ ለመጠበቅና ስርጭትን ለመግታት በሚል በተወሰዱ እና በመወሰድ ላይ ባሉ እርምጃዎች ምጣኔሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ክፉኛ ተዳክመዋል ያለው ባንኩ ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ምጣኔ ሃብታዊ ልሽቀት ውስጥ መውደቋን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በግዙፍነታቸው ሊጠቀሱ የሚችሉ የዓለም ክፍለ ኢኮኖሚዎች እ.ኤ.አ ከ1870 ወዲህ አይተውት የማያውቁት ዓይነት የነፍስ ወከፍ ገቢ እጦት እንደገጠማቸውም ነው ያስቀመጠው፡፡
ወረርሽኙን ተከትሎ ያጋጠመው የፍላጎት መቀዛቀዝ ብቻ አይደለም፡፡ የፍላጎትና አቅርቦት፣የንግድ እና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ተዛብተዋል፡፡
በዚህም አደጉ የሚባሉት ሃገራት ምጣኔ ሃብት የ7 በመቶ፣ በማቆጥቆጥ ላይ ያለ ገበያን ለመፍጠር የሚታትሩ ታዳጊ ሃገራት ደግሞ የ2 ነጥብ 5 በመቶ ማሽቆልቆል እንደሚገጥመው ተገምቷል፡፡
በ3 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚቀንስ የሚጠበቀው ነፍስ ወከፍ ገቢም በርካታ ዜጎችን ለከፋ ድህነት ሊዳርግ ይችላል፡፡
በተለይ የዓለም አቀፍ ገበያን የተንተራሰ በወጪ ንግድ፣ በቱሪዝም እና በውጭ የፋይናንስ ምንጮች ላይ የተመሰረተ ምጣኔ ሃብት ያላቸው ሃገራት በወረርሽኙ ጫና ክፉኛ ተንገዳግደዋል፡፡
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገራትም ከዚሁ ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት አላመለጡም፡፡ እንቅስቃሴያቸውም ተዳክሟል፡፡ የቀጣናው ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በ2 ነጥብ 8 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል ይጠበቃል በሪፖርቱ እንደተቀመጠው ከሆነ፡፡
ኢትዮጵያም ከነዚሁ የቀጣናው ሃገራት መካከል ነች፡፡ ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ የከፋ ችግር ባይገጥማትም የቱሪዝም እንቅስቃሴዋ ግንእጅጉን ተዳክሟል፡፡
ትናንት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ቆይታ የነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይህንኑ መግለጻቸውና ለማነቃቃት እንደሚሰራ መናገራቸውን አል ዐይን አማርኛ መዘገቡም የሚታወስ ነው፡፡
ምጣኔ ሃብቷ በዚህ ፈታኝ ችግር ውስጥ ሆኖም ቢሆን በ6 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
በአደጉ ሃገራት የተጀመረው ተጥለው የነበሩ ገደቦችን የማንሳት፣ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲነቃቁ የማድረግ ጅምር ጥረቶች ተሟሙቀው መቀጠል የሚችሉ ከሆነ ማሽቆልቆሉ በአጋማሽ የአመቱ ወራት ሊቀንስ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ይህም በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ማለትም በ2021 የዓለም ምጣኔ ሃብት አገግሞ በ4 ነጥብ 2 በመቶ ሊያድግ እንደሚችልም ተተንብይዋል፡፡