ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ታሪክ 900 ግቦችን በማስቆጠር የመጀመርያው ሰው ሆነ
ሮናልዶ በኔሽንስ ሊግ ፖርቹጋል ከክሮሽያ ባደረገችው ግጥሚያ ነው 900ኛ ግቡን ያስቆጠረው
ለክለብ እና ለብሔራዊ ቡድን በሚደረጉ ጨዋታዎች 800 ግቦችን በመሻገር ሮናልዶ ቀዳሚ መሆንም ችሏል
ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በእግር ኳስ ህይወት ዘመኑ 900 ግቦችን በማስቆጠር የመጀመርያው ሰው መሆኑን አረጋግጧል።
የአምስት ጊዜ ባላንዶር አሸናፊው ሮናልዶ ትላንት ምሽት በአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ጨዋታ ፖርቹጋል እና ክሮሽያ ባደረጉት ግጥሚያ በ34ኛው ደቂቃ ያስቆጣርት ግብ ታሪክ የጻፈባት ሆናለች።
ግቡን ካስቆጠረ በኋላ እጆቹን ፊቱ ላይ ጭኖ ስሜታዊ ሆኖ የታየው ሮናልዶ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በእግር ኳስ ህይወቱ ባሳካቸው ውጤቶች ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።
“ይህ ለእኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው እዚህ ነጥብ ላይ ለመድረስ ለረጅም ጊዜ ስጠብቅ ቆይቻለሁ፤ እግር ኳስ ከማቆሜ በፊት ይህን ድል ማሳካት እፈልግ ነበር ታሪኩን በብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታ ላይ ስላስመዘገብኩ ደግሞ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
በትናንትናው እለት ፖርቹጋል 2ለ1 በሆነ ውጤት ክሮሽያን በረታችበት ግጥሚያ ሮናልዶ ያስቆጠረው ግብ ለብሔራዊ ቡድኑ 131ኛ ግብ ሆኖ ተመዝግቦለታል።
ለክለቦች ባደረጋቸው ጨዋታዎች 769 ጎሎችን ያስቆጠረው ተጫዋቹ በአጠቃላይ በእግር ኳስ ህይወቱ 900 ኳሶችን ከመረብ በማገናኝት በእግር ኳስ ታሪክ የመጀመርያው ሰው ሆኗል።
እንደ ኦሎምፒክ መረጃ ከሆነ ደግሞ ለክለብ እና ለብሔራዊ ቡድን በሚደረጉ ጨዋታዎች 800 ግቦችን በመሻገር ሮናልዶ የመጀመርያው ሰው መሆን ሲችል በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ባስቆጠራቸው 141 ጎሎች ከያዘው ክብረወሰን ጋር የሚታከል ነው።
ተፎካካሪው ሊዮኔል ሜሲ 842 ግቦችን በማስቆጠር ሁለተኛ ሲሆን ብራዚላዊው የቀድሞ የእግር ኳስ ፈርጥ ፔሌ በ765 ጎሎች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ ሲፒ በ2003 ማንችስተር ዩናይትድን ከተቀላቀለ በኋላ ለቡድኑ 145 ግቦችን ፣ በስፔን ላሊጋ በሪያል ማድሪድ በነበሩት ጨዋታዎች 450፣ ለጁቬንቱስ 101 እንዲሁም አሁን እየተጫወተበት ለሚገኝው የሳኡዲ አረብያው ክለብ አልናስር 68 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
በቅርቡ በከፈተው የዩትዩብ ቻናል ከቀድሞ የቡድን አጋሩ እና የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሪዮ ፈርዲናንድ ጋር ባደረገው ቆይታ በእግር ኳስ ህይወቱ አንድ ሺህ ግቦችን ማግባት እንደሚፈልግ ተናግሯል።