ሮናልዶ ስለ2026ቱ የአለም ዋንጫ ተሳትፎ እቅዱ ምን አለ?
ፖርቹጋላዊው ኮከብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአለማቀፍ ጨዋታዎች ራሱን ሊያገል ነው በሚል የወጡ ዘገባዎችን ውድቅ አድርጓል
ፖርቹጋል በአውሮፓ ኔሽንስ ካፕ ከነገ በስቲያ ከክሮሽያ ጋር ትጫወታለች
ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአለማቀፍ የእግርኳስ መድረክ ለሀገሩ መሰለፉን እንደሚቀጥል ተናገረ።
ሮናልዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአለማቀፍ የእግርኳስ ጨዋታዎች መሰለፍ ያቆማል በሚል ባለፈው ሳምንት የወጡ ዘገባዎችን ውድቅ አድርጓል።
የሳኡዲው አል ናስር ክለብ ተጫዋች ከፖርቹጋል የቴሌቪዥን ጣቢያ “ናው” ጋር ባደረገው ቆይታ “ከሁለት ወይም ሶስት አመት በኋላ ምናልባት እግርኳስ ላቆም እችላለሁ” ማለቱ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የ39 አመቱ አጥቂ የእግርኳስ ህይወቱ ወደመጠናቀቁ መቃረቡን ያሳያል ቢባልም፥ የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ግን “በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአለማቀፍ ጨዋታዎች ራሴን አላገልም” ብሏል ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ።
“ከፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ጋር እለያያለሁ የሚል ሀሳብ ወደ አዕምሮዬ መጥቶ አያውቅም፤ በተቃራኒው ሀገሬን በጥሩ ብቃት ለመወከል ከፍተኛ ብርታት አለኝ” ሲልም ነው ያከለው።
ፖርቹጋል በ2018 መካሄድ በጀመረው የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ከክሮሺያ፣ ስኮትላንድ እና ፖላንድ ጋር ተደልድላለች። የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋንም ከነገ በስቲያ ከክሮሽያ ጋር ታደርጋለች።
የኔሽንስ ሊግ ሲጀመር ሀገሩን በአምበልነት በመወከል ለድል ያበቃው ሮናልዶም ሀገሩ ሁለተኛውን ዋንጫ እንድታነሳ የማድረግ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው መናገሩን ነው ጎል ስፖርት ያስነበበው።
ሮናልዶ አሜሪካ፣ ካናዳና ሜክሲኮ ከሁለት አመት በኋላ በሚያዘጋጁት የአለም ዋንጫ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ተጠይቆ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።
“በአሁኑ ወቅት ጥሩ አቋም ላይ እገኛለሁ” ያለው ተጫዋቹ የመጨረሻው ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው የአለም ዋንጫ መሳተፍ ስለመፈለጉ ከመናገር ተቆጥቧል። ይልቁንም “አሁን ባለሁበት ወቅታዊ ሁኔታ መዝናናትን እመርጣለሁ” ብሏል።
“ኳስ እስከማቆምበት ጊዜ ድረስ ሁሌም እንደ ጀማሪ ተጫዋች መጣር እንዳለብኝ አምናለሁ” የሚለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ፥ ለፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ትልቅ ሀብት እንደሆነ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ ጭምር እንደሚያምኑ አብራርቷል።
“ለብሄራዊ ቡድኑ (ፖርቹጋል) ምንም የማልፈይድ መሆኔ ሲሰማኝ ራሴን በፍጥነት ከቡድኑ አገላለሁ” በማለትም በ41 አመቱ ከብሄራዊ ቡድኑ በክብር ራሱን ያገለለውን የቀድሞ የቡድን አጋሩን ፔፔ አስታውሷል።
“እንደሁልጊዜውም ማን እንደሆንኩ፣ ምን መስራት እንደምችልና መስራት እንዳለብኝ ጠንቅቄ አውቃለሁ” ያለው ፖርቹጋላዊው ኮከብ፥ ተሳክቶለት በ2026ቱ የአለም ዋንጫ ከተሳተፈ 41ኛ አመቱ ይይዛል።
ባለፈው ሳምንት በሻምፒዮንስ ሊጉ የምንጊዜም ግብ አስቆጣሪ ተብሎ ልዩ ሽልማት የተበረከተለት ሮናልዶ ጀርመን ባስተናገደችው የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ አንድም ጎል አለማስቆጠሩ ትችት እንዳስነሳበት ይታወሳል።
“ያለሂስ ለውጥ አይመጣም” ባዩ ፖርቹጋላዊ፥ በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ባሳየው ብቃት የሚነሳበት የበረታ ትችት እንደማያስጨንቀው ገልጿል።
ሮናልዶ ለሀገሩ ፖርቹጋል 212 ጊዜ ተሰልፎ 130 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።