ተጫዋቹ በቫይረሱ ምክንያት የብሔራዊ ቡድን እና የክለብ ጨዋታዎች ያመልጡታል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኮሮና ሲያዝ ሌሎች የቡድኑ አባላት ነጻ ሆነዋል
የፖርቹጋል እና የጁቬንቲዩስ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኮሮና ቫይረስ መያዙ ተዘገበ፡፡ ተጫዋቹ በቫይረሱ መያዙን የፖርቹጋል እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የ35 ዓመቱ ሮናልዶ በቫይረሱ መያዙ ቢረጋገጥም ምንም አይነት ምልክቶችን እንዳላሳየ እና ከብሔራዊ ቡድኑ ተቀንሶ ራሱን እንዲያገል ወደ ቤቱ መሔዱን የስካይ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ሮናልዶ በኮሮና በመያዙ ምክንያት በአውሮፓ ሀገራት ሊግ ምድብ ኤ3 ፖርቹጋል ከስዊዲን ነገ በሊዝበን የሚያደርጉት ጨዋታ ያመልጠዋል፡፡
ሌሎች በውድድሩ የሚሳተፉት የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አባላት ሁሉም ዛሬ ተመርምረው ከቫይረሱ ነጻ ሆነዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ እንደገለጸው ሮናልዶ ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ተከትሎ ነው ሁሉም ተጫዋቾች በድጋሚ ምርመራ ያደረጉት፡፡
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ እና የሪያል ማድሪድ አጥቂ ሮናልዶ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ዕረፍት ወቅት በአውሮፓ ሀገራት ሊግ በተካሔዱት በሁለቱም የፖርቹጋል ጨዋታዎች ላይ ተሳትፏል፡፡
ተጫዋቹ በአውሮፓውያኑ መስከረም 27 ከሮማ ጋር 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ያስቆጠራቸውን ሁለት ጎሎች ጨምሮ በዚህ የውድድር ዘመን በእያንዳንዱ የሴሪ ኤ ጨዋታ ላይ ጎል አስቆጥሯል፡፡
በቫይረሱ ምክንያት በሴሪኤ ውድድርም ጁቬን ቅዳሜ ወደ ክሮቶን አቅንቶ ከክለቡ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ እንዲሁም በሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ መክፈቻ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ ከዳይናሞ ኬቭ ጋር በሚኖረው ጨዋታ አይሰለፍም፡፡
በፖርቹጋል እስካሁን 89,121 ሰዎች በኮሮና ሲያዙ 2,110 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 54,047 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡ የሀገሪቱ የሕዝቧ ብዛት 10.1 ሚሊዮንእንደሆነ ይገመታል፡፡
ሀገሪቱ ቫይረሱ በተከሰተበት ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል የሰጠችው ፈጣን ምላሽ ቢደነቅም ዘ ናሺናል እንደዘገበው ኋላ ላይ ግን ድክመት ታይቶባት የተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል፡፡