ፖርቹጋልን ጨምሮ ስድስት የአውሮፓ ሃገራት ጥለውት የነበረውን እገዳ በዚህ ሳምንት ያነሳሉ
ፖርቹጋልን ጨምሮ ስድስት የአውሮፓ ሃገራት ጥለውት የነበረውን እገዳ በዚህ ሳምንት ያነሳሉ
ጣልያንን ጨምሮ ስድስት የአውሮፓ ሃገራት የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት በሚል ጥለውት የነበረውን እገዳ በዚህ ሳምንት ያነሳሉ ተብሏል፡፡
ሃገራቱ ፖርቱጋል ፣ጣልያን፣ ቤልጂዬም፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ እና አየርላንድ ናቸው እንደ ሲ.ኤን.ኤን ዘገባ፡፡
በሙዚየሞችና ፓርኮች ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ እገዳ ያነሳችው ጣልያን ተወዳጁን የሴሪዓ የእግር ኳስ ውድድር በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ለማስጀመር ዝግጅት ላይ ናት፡፡
በቤልጂዬም ከፊታችን አርብ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፡፡ ካፌና ሬስቶራንቶችን ጨምሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መክፈት የጀመረችው ኔዘርላንድም በመምህራንና በተማሪዎች መካከል የአንድ ሜትር ተኩል ርቀት እንዲኖር በማሳሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶቿን ለመክፈት ተዘጋጅታለች፡፡
በስዊዘርላንድ ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ እስከ 3 መቶ ታዳሚዎች የሚገኙባቸው የተለያዩ መዝናኛ እናበቤተሰብ ደረጃ የሚካሄዱ ስነ ስርዓቶች ተፈቅደዋል፡፡
እገዳዎችን ማቅለል በጀመረችው ፖርቹጋልም የስራ እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ እየተነቃቁ ነው፡፡ ቴአትር እና ሲኒማ ቤቶች በተከፈቱባት የማዴራ ደሴት በምሽት መዝናናት ይቻላል፡፡ ወደ ሃገሪቱ ሚገቡ ቱሪስቶችም ተለይተው እንዲቆዩ አይጠየቁም፡፡
ዜጎች ከቤታቸው እስከ 20 ኪሎ ሜትሮች ርቀው መጓዝ እንደሚችሉ በፈቀደችው አየርላንድም አነስተኛ የችርቻሮ ተቋማት እና የህዝብ በተ መጻህፍቶች ይከፈታሉ ተብሏል፡፡
በአውሮፓ እስካሁን 2 ሚሊዬን 47 ሺ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና 176 ሺ ገደማ ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ቀደም ሲል በተጠቀሱት ስድስት ሃገራት ደግሞ እስካሁን 430 ሺ ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ54 ሺ በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡