እስካሁን 56 ሰዎችን የገደለው የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት እየተዛመተ ነው፡፡
በቻይና ዉሀን ከተማ የተከሰተው ኮሮና ቫይረስ እስካሁን በትንሹ 56 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡ ሁሉም ሞት የተከሰተው እዚያው ቻይና ውስጥ ነው፡፡
በቻይና ብቻ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 2,000 ገደማ ሲያሻቅብ ከቻይና ውጭ ደግሞ በ13 ሀገራት ከ40 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 49 ሰዎች በተደረገላቸው የህክምና ክትትል መዳናቸውን ሲጂቲኤን የዘገበ ሲሆን ይሄም አንድ ተስፋ ሰጪ ሁነት ሆኗል፡፡
“ቻይና እጅግ አስከፊ ችግር ዉስጥ ትገኛለች” ያሉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒነግ፣ ቫይረሱን መቆጣጠር ሀገሪቱ ቅድሚያ የምትሰጠው ወቅታዊ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በየትኛውም የስልጣን እርከን የሚገኙ የቻይና ባለስልጣናት የህዝቡን ደህንነት በማስቀደም ቫይረሱን መቆጣጠር ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉም ፕሬዝዳንቱ ትናንት የኮሚዩኒስት ፓርቲውን የፖለቲካ ቢሮ ቋሚ ኮሚቴ አባለት ሰብስበው በጉዳዩ ላይ ባወያዩበት ወቅት አሳስበዋል፡፡
ሀገሪቱ በሽታውን ለመቆጣጠር እና ስርጭቱን ለመግታት በምታደርገው ጥረት ቫይረሱ ሰፋ ብሎ የታየባቸውን አካባቢዎች መዝጋቷን የቀጠለች ሲሆን 30 ከተሞች የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፡፡
በማእከላዊ ቻይና ሁቤይ ግዛትና አካባቢው የሚገኙ 63 ሚሊዮን ያክል ሰዎች እስካሁን ከአካባቢያቸው እንዳይወጡ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡
አብዛኛው የቫይረሱ ተጠቂዎች በሚገኙበት የሁቤይ ግዛት ዉሀን ከተማ ከሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለ 1,000 አልጋዎች ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ ሆስፒታል ግምባታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
1,300 ሰዎችን የሚያስተናግድ ሁለተኛ ተመሳሳይ ሆስፒታልም እዚያው ዉሀን ከተማ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ይገነባል ተብሏል፡፡
ይሁን እንጂ በቫይረሱ ላይ ጥናት እያደረጉ የሚገኙ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ቻይና ቫይረሱን መቆጣጠር ሊከብዳት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
የቫይረሱ አዝማሚያ ያሰጋት አሜሪካ በዉሀን ቆንስላዋ እና በቻይና አስጊ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎቿን በቀጣዩ ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም ለነርሱ በተዘጋጀ ልዩ በረራ ወደ ሳን ፍራሲስኮ እንደምትመልሳቸው አስታውቃለች፡፡
ከዋናው የቻይና ግዛት ውጭ ሆንግ ኮንግ(5) ፣ ማካኦ(5) ፣ታይላንድ(5) ፣ አውስትራሊያ (4)፣ ማሌዢያ(4)፣ ሲንጋፖር (4)፣ ፈረንሳይ (3)፣ ደቡብ ኮሪያ (3)፣ ጃፓን(3) ፣ዩኤስኤ (3)፣ታይዋን(3)፣ ቬትናም(2) እና ኔፓል(1)፣ ካናዳ (1) ምልክት የታየባቸው ናቸው፡፡
ከባድ ጉንፋን፣ ሳል፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ ህመም፣ለመተንፈስ መቸገር፣ ትኩሳት እና አጠቃላይ የህመም ስሜት የቫይረሱ ምልክቶች ናቸው፡፡ ቫይረሱ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ሲደርስ የሳምባ ምች እና የኩላሊት ህመም አስከትሎ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡
መነሻውን ከእንስሳት ያደረገው ቫይረሱ ተላላፊ ከሰው ወደሰውም የሚተላለፍ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄን ማድረግ የተለየ ምልክት የሚታም ከሆነ መታከም የሚገባ ሲሆን የአፍና አፍንጫ አካባቢ መሸፈኛ (ማስክ) መጠቀም ንክኪንም መቀነስ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ የአለማችን አየር መንገዶች፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል፣ በተለይ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን መመርመር ጀምረዋል፡፡
ሲጂቲኤን፣ሲኤንኤን እና ሮይተርስ የዜናው ምንጮቻችን ናቸው፡፡