ተዘግቶ የነበረው የደብረ ብርሃን-ደሴ መንገድ ከነገ ጀምሮ ክፍት እንደሚሆን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ
ኮማንድ ፖስቱ ባለፈው የካቲት 18 መንገዱን የዘጋው "ጽንፈኛ" በሚላቸው የፋኖ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ነበር
የማዕከላዊ ሽዋ ኮማንድ ፖስት ተዘግቶ የነበረው ከደብረ ብርሃን- ደሴ እና ከደሴ- ደብረ ብርሃን የሚወስደው ዋናው መንገድ ከነገ ጀምሮ ለተጓዦች ክፍት ይደረጋል ብሏል
ተዘግቶ የነበረው የደብረ ብርሃን-ደሴ መንገድ ከነገ ጀምሮ ክፍት እንደሚሆን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ።
በሰሜን ሽዋ ዞን ኮሙኒኬሽን በኩል የወጣው የማዕከላዊ ሽዋ ኮማንድ ፖስት መግለጫ ተዘግቶ የነበረው ከደብረ ብርሃን- ደሴ እና ከደሴ- ደብረ ብርሃን የሚወስደው ዋናው መንገድ ከነገ ጀምሮ ለተጓዦች ክፍት ይደረጋል ብሏል።
ኮማንድ ፖስቱ ባለፈው የካቲት 18 መንገዱን የዘጋው "ጽንፈኛ" በሚላቸው የፋኖ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ነበር።
መንገዱ የሚከፈተው "የቀጠናው የሰላም ሁኔታ ካሳየው መሻሻልና ከህብረተሰቡ ጥያቄ በመነሳት" መሆኑን የገለጸው ኮማንድ ፖስቱ ከነገ መጋቢት 28፣2016 ዓ.ም ጀምሮ ክፍት ይሆናል ብሏል።
ትራስፖርት አገለግሎቱ በመቋረጡ ምክንያት በተለይ ህክምና የሚያስፈልጋቸው የአካባባው ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸው በቅርቡ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረው ነበር።
የፌደራል መንግስት ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር የክልል ልዩ ኃይሎችን ማፍረሱን ተከትሎ በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የትጥቅ ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በመደበኛው የህግ ማስከበር መቆጣጠር እንደማይቻል የገለጸው መንግስት በሐምሌ መጨረሻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በማወጅ ክልሉ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ አድርጓል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማዕከላዊ ሽዋ ኮማንድ ፖስት የሰሜን ሽዋ ዞንን የጸጥታ ሁኔታ የሚቆጣጠር አካል ነው።
አዋጁ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ በአራት ወራት ቢራዘምም በፌደራል መንግስት የፈጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ያለው ግጭቱ አሁንም አልቆመም።
በግጭቱ አውድም መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየደረሰ እንደሆነ የመብት ድርቶች እየገለጹ ይገኛሉ።
አምነተስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ባወጣው ሪፖርቱ መንግስት አዋጁን ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት እና ለማሰር ተጠቅሞበታል የሚል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
በተመሳሳይ ሂማን ራይትስ ዎች በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫው የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በክልሉ ከነሀሴ 2015 ጀምሮ ንጹሃንን ከህግ አግባብ ውጭ መግደላቸውን እና ንብረት ማውደማቸውን ገልጿል።
አዋጁ ተፈጻሚ በሆነበት ወቅት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ግድያ እና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን የሚያወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንም(ኢሰመኮ) የአዋጁን መራዘም በሰብአዊ መብት ላይ ጥሩ አንድምታ የለውም በማለት ተችቶታል።