ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ
በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ላልተወሰነ ጊዜ ለሥራ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ተከልክሏል
ህብረተሰቡ እራሱን፣ ቤተሰቡንና ልጆቹን ከማንኛውም ሰልፍና ሁከትና ከሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች እንዲጠብቅ ግብረ ኃይሉ አሳስቧል
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ይህን እኩይ የኢትጵያን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ገለፀ።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ማሻውን ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ለየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም የተጠራው ሰልፍ እንዲቀር መወሰናቸው ከሀገር ህልውናና ከዜጎች ደኅንነት መጠበቅ አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በማስታወቅ አክብሮቱን ገልጿል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ፤ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የተነሳውን አጀንዳ ሽፋን አድርገው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች በሰልፍ ሰበብ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች መኖራቸው እንደተደረሰበት አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም የጋራ ግብረ-ኃይሉ የኢትዮጵያን ህልውናና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ፣ለማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል።
በመሆኑም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ይህን እኩይ ሴራቸውን በማክሸፍ የኢትጵያን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ገልጿል።
በዚህ መሰረትም በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ለሥራ ከተፈቀደላቸው የፀጥታና ደኅንነት አካላት ውጪ ማንኛውም ሰው የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን የተቋቋመው የጋራ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አስታውቋል።
እንዲሁም ኅብረተሰቡ እራሱን፣ ቤተሰቡንና ልጆቹን ከማንኛውም ሰልፍ ወይም ሁከትና ግርግር ከሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች እንዲጠበቁ ማድረገ እንደሚገባው የጋራ ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል።
የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ፤ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ የሚያደርጉትን ጥረቶችን ለማምከን የተቀናጀ ስምሪት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል።
ከእምነት ተቋማት ደኅንነት ጋር በተያያዘ ተገቢው ጥበቃ የሚደረግ በመሆኑ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ምንም አይነት ስጋት እንዳያድርባቸውም አስገንዝቧል።