ተመድና የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ አዲስ ሰላም አስከባሪ ሃይል እንዳታሰማራ እንዲያግዱ ተጠየቀ
የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል “የጦር ወንጀል” መፈጸማቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል
የሰብአዊ መብት ተቋሙ የመንግስታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች የተፈጸሙ ጥፋቶችን መመርመር እንዲጀምርም ነው የጠየቀው
የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ነሃሴ 2015 ጀምሮ ከህግ አግባብ ውጪ ንጹሃንን መግደላቸውንና ንብረት ማውደማቸውን ሂዩማን ራይትስ ዎች ገለጸ።
በመራዊ ከተማ በጥር ወር 2016 በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ “የጦር ወንጀል” ነው ያለው የሰብአዊ መብት ተቋሙ ከ20 በላይ ሰዎችን አናግሮና ከጥቃቱ በኋላ የወጡ የቪዲዮ ምስሎችን በጥልቀት በመመርመር ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።
ይህን ግኝቱንም ለኢትዮጵያ መንግስት ቢይቀርብም እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጠው ነው በዛሬው እለት የገለጸው።
“የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል ንጹሃን ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ ግድያ መንግስት ከሚያቀርበው ህግና ስርአትን የማስከበር ጥረት ጋር የሚጋጭ ነው” ብለዋል የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር ላቲቲያ ባደር።
የኢትዮጵያ የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ጦርነት ከጀመሩ አንስቶ ንጹሃን ከህግ አግባብ ውጭ መገደላቸው እንደቀጠለ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሪፖርቱ የመራዊ ከተማን እንደ አብነት አነሳ እንጂ በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞችም በንጹሃን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሟል።
ከባህርዳር በ30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው መራዊ ወታደሮች በርካታ ንጹሃንን ከመግደላቸው ባሻገር በቤቶች፣ ሆቴሎች እና የንግድ ተቋማት ዝርፊያ መፈጸማቸውንና በጥቂቱ 12 ባጃጆችን ማቃጠላቸውን የአይን እማኞች ነግረውኛል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች።
በመራዊ ምን ያህል ንጹሃን እንደተገደሉ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ያነሳው ተቋሙ፥ ከ80 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን ከሶስት ምንጮች መስማቱንም በሪፖርቱ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በመንገድ ላይ አስከሬናቸው የወደቁ ሰዎችን እንዳይቀበሩም ቤተሰቦቻቸውን ሲከለክሉ እንደነበር በቀደመው ሪፖርቱ ማንሳቱ የሚታወስ ነው።
በአማራ ክልል ከህግ አግባብ ውጪ ሆን ተብለው የሚፈጸሙ የንጹሃን ግድያዎች፣ ዝርፊያ እና የንብረት ውድመት በአለማቀፉ የጦር ህግ እንደ ጦር ወንጀል የሚቆጠሩ መሆናቸውንም ነው ያነሳው።
የኢትዮጵያ መንግስት ግን በመራዊ በሚገኝ ወታደራዊ ጣቢያ በፋኖ ታጣቂዎች ለተፈጸመበት ጥቃት አጻፋዊ እርምጃ መውሰዱን እንጂ በንጹሃን ላይ ግድያ እንዳልፈጸመ መግለጹ ይታወሳል።
አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት ባወጡት መግለጫ በመራዊ ንጹሃን በገፍ የተገደሉበትን ጥቃት ማውገዛቸውና በገለልተኛ አካል ምርምራ እንዲጀመር መጠየቃቸው አይዘነጋም።
ሂዩማን ራይትስ ወች በዛሬው መግለጫው በአማራ ክልል በንጹሃን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት እና የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ምርመራ እንዲጀምሩ ጠይቋል።
በንጹሃን ላይ ግድያ እና ዝርፊያ የፈጸሙ የጸጥታ አካላት ተጠያቂ አለመደረጋቸው ጥፋቱ እንዲቀጥል ማድረጉን በመጥቀስም በገለልተኛ አካል ምርመራ ተደርጎ ተጠይቂነት ሊሰፍን ይገባል ብሏል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትም በአማራ ክልል በንጹሃን ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆምና ፍትህ እንዲሰፍን ጫና ማድረግ እንዳለባቸው ነው የጠየቀው።
“በኢትዮጵያ ንጹሃን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በጅምላ የመገደላቸው ጉዳይ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ የየእለት ክስተት ሆኗል” የሚሉት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር ላቲቲያ ባደር፥ የኢትዮጵያ አጋር ሀገራትና ተቋማት ይህን ፈታኝ ጉዳይ ሊያስቆሙ ይገባል ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ አዲስ ሰላም አስከባሪ ሃይል እንዳታሰማራ በማገድ በንጹሃን ግድያ የተሳተፉ አካላት ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ይወጡ ዘንድም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በፊት ባወጣቸው መግለጫዎች በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ የጸጥታ ሃይሎች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ ቢገልጽም እስካሁን የተወሰደውን እርምጃ በዝርዝር ይፋ አላደረገም።