ማሊ ወታደሮቹ ያለእኔ እውቅና ስለገቡ ለቀው እንዲወጡ አዛለች
ማሊ ሳይፈቀድላቸው ወደ ግዛቷ የገቡ የዴንማርክ ወታደሮች ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች፡፡
ከምዕራብ አፍሪካ አገራት በመነሳት አሸባሪዎች ወደ አውሮፓ አየገቡ አደጋ ይፈጥራሉ በሚል ነበር የአውሮፓ ሀገራት ጦራቸውን ማሊን ጨምሮ ወደ ሳህል ቀጠና የላኩት፡፡
ከአምስት ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት የሚነገርለት የአውሮፓ ጦር ፈረንሳይ ይሄንን ጦር በበላይነት በማስተባበር ላይ ትግኛለች፡፡አሁን ደግሞ ዴንማርክ ባለፈው ሳምንት 90 አባላት ያሉት ጦሯን ወደ ማሊ ማስገባቷን አስታውቃለች፡፡
የማሊ መንግስት ግን ዴንማርክ ጦሯን ወደ ማሊ እንድታስገባ ሳይፈቀድላት አስገብታለች፣ ስለ ጉዳዩ የምናውቀው ነገር የለም ጦሩ ለምን እንደገባ አናውቅም ስትል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቼኩል ሜጋ በኩል አስታውቃለች፡፡
ዴንማርክ በማሊ ያስገባችውን ጦር እንድታስወጣ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፕ ኮፎድ በበኩላቸው ጦራችንን ያስገባነው በቀረበልን ግብዣ መሰረት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የማሊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት የማይታመን ነገር አለው ያሉት ሚኒስትሩ የዴንማርክ ጦር እንደማንኛውም የአውሮፓ ጦር ተጋብዞ ነው በምዕራብ አፍሪካ ተሰማርቷልም ብለዋል፡፡
በፈረንሳይ አስተባባሪነት የሚመራው ከአውሮፓ ሀገራት የተውጣጣው ጦር ከተሰማራ ጊዜ በኋላ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት አክራሪ ጽንፈኞች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እየጨመረ ሄደ እንጂ መቀነስ አላሳየም፡፡
የአካባቢው አገራት ዜጎችም በፈረንሳይ አስተባባሪነት የሚመራው የአውሮፓ ጦር ሽብርተኛ ቡድኖችን እየደገፈ ነው፣ ደካማ መንግስታት እንዲፈጠሩ እያደረገ ነው እና መሰል ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት በሀገራቸው የሰፈረው ጦር አገራቸውን ለቆ እንዲወጣ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
የማሊ መንግስትም ጦሩ ሀገሯን ለቆ እንዲወጣ በይፋ የጠየቀ ሲሆን ድርጊቱ ፈረንሳይን እና ሌሎች የአውሮፓ አገራትን አስቆጥቷል፡፡
ማሊ ከሩሲያው ዋግነር ከተሰኘው ቅጥረኛ ወታደሮችን ወደ ሀገሯ ማስገባቷን ተከትሎ በተለይም ከአውሮፓ ሀገራት ትችቶችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡