በጦር ሰፈሩ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እስካሁን ይፋ አልሆነም
በማሊ ያለው የፈረንሳይ የጦር ሰፈር በሮኬት መመታቱ ተዘግቧል፡፡
ፈረንሳይ በማሊ ውስጥ በርካታ የጦር ሰፈሮች ያሏት ሲሆን በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ያለው የጦር ክምፕ ዛር ረፋድ የሮኬት ጥቃት እንደደረሰበት ተገልጿል፡፡
ልዩ ስሙ ጋኦ በሚባል ስፍራ ያለው የፈረንሳይ ጦር በደረሰበት የሮኬት ጥቃት ምን ያህል እንደተጎዳ፣ጥቃቱን ማን እንዳደረሰው እስካሁን አልተገለጸም፡፡
በዚህ የጦር ሰፈር ከ24 በላይ የፈረንሳይ ጦር እንደሰፈረ የተገለጸ ሲሆን ተልዕኳቸውን በመወጣት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
የማሊ መንግስት የፈረንሳይ ጦር ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ የጠየቀች ሲሆን በምትኩ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ወደ ሀገሯ ማስገባቷ ፈረንሳይን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትን አስቆጥቷል፡፡
ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በራካታ የጦር ካምፕ ያላት ሲሆን የአካባቢው ሀገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፈረንሳይ ጦር አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ፈረንሳይ እና ሌሎቸ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ጦራቸውን ወደ ምዕራብ አፍሪካ የላኩት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ጽንፈኛ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ በሚል ቢሆንም ማሊን ጨምሮ የአካባቢው ሀገራት የሽብር ቡድኖች ጥቃት እየጨመረ መሄዱን ይናገራሉ፡፡
በዚህም መሰረት ማሊ፣ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በፈረንሳይ አስተባባሪነት በምዕራብ አፍሪካ ያለው ጥምር ጦር ሀገራቸውን ለቀው እንዲወጡ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ፈረንሳይ እና ስዊድንም በምዕራብ አፍሪካ ያሰማሩትን ጦር እንደሚቀንሱ እና እንደሚያስወጡ መናገራቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡